ከማል ኢብራሂም በአዲሱ ክለቡ ሩቅ ያልማል 

የ2015 የአውስትራሊያ ኤንፒኤል ቪክቶሪያ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ከማል ኢብራሂም ከአዲሱ ክለቡ ጋር የተሻለ ቆይታ እንደሚኖረው ለኤምፉትቦል ድረ ገፅ ገለፀ፡፡ 

የመስመር አማካዩ ከማል ፖርት ሜልቦርን ሻርክስን ለቆ ወደ ሻምፒዮኖቹ ቤንትሊጅ ግሪንስን ተቀላቅሏል፡፡ ከማል ለፖርት ሜልቦርን ሻርክስ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በ28 ጨዋታዎች 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

የ24 ዓመቱ ከማል ለድረ ገፁ በሰጠው አስተያየት ከፖርት ሜልቦርን ሻርክስ የተለያየበት ወቅት ትክክለኛው ግዜ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “በፖርት ሜልቦርን ላለፉት ሶስት ዓመታት ጥሩ ግዜ አሳልፊያለው፡፡ የለቀቀኩበት ግዜ ትክክል ነበር፡፡ የቤንትሊጅ ግሪንስ አጨዋወት ፍልስፍና አደንቃለው፡፡ እንደሚሰማኝ ከሆነ በዚሁ ክለብ ጥሩ የሆነ እግርኳስ መጫወት እችላለው፡፡”

የቀድሞ የአውስትራሊያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ከማል በግሉ አስደናቂ የውድድር ዓመት ማሳለፉ ሌሎች ክለቦች የፖርት ሜልቦርን ሻርክስን በር እንዲያንኳኩ አድርጓል፡፡ “ቤንትሊጅ ግሪንስ ሊያስፈርሙኝ እንደሚፈልጉ ሲነግሩኝ በፖርት ሜልቦርንስ በኩል ችግር አልነበረም፡፡ ፖርት ሜልቦርን ቦርድ ፍላጎቴን ተረድተው ወደ ቤንትሊጅ ግሪንስ ሄጂያለው፡፡ ከፖርት ሜልቦርን ጋር የተለያየነውን በስምምነት እና ሰላማዊ መንገድ ነው፡፡”

ከማል ለቤንትሊጅ ግሪንስ የመጀመሪያ ጨዋታውን በወዳጅነት ጨዋታ ከሜልቦር ሲቲ ጋር በዝግ ስታዲየም አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ አሁንም በኤ ሊግ ክለቦች እይታ ውስጥ አለመግባቱ እንዳበሳጨው ተናግሯል፡፡ “ባለፈው ዓመት ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩ፡፡ የኤንፒኤል ቪክቶሪያ ሊግ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ነበርኩ ነገርግን አንድም የኤ ሊግ ክለብ ለሙከራ አልጠራኝም፡፡”

የኤ ሊግ ክለብ በሆነው ሜልቦርን ሃርትስ (የአሁኑ ሜልቦርን ሲቲ) ጋር የሶስት ዓመት ቆይታ የነበረው ከማል የኤ ሊግ ክለቦች አሁን ተጫዋቾችን ለመመልመል ወደ ኤንፒኤል ቪክቶሮያ ሊግ መመልከት መጀመራቸው እንደበጎ ጎን ያነሳል፡፡ “በሊጉ ተጫዋቾች ለመመልመል መፈለጋቸው ጥሩ ነው፡፡ የአሁኑ የውድድር ዘመን ጥሩ ተንቀሳቅሼ ወደ ኤ ሊግ ክለብ መዛወር ፍላጎቴ ነው፡፡”

አውስትራሊያን በወጣት ብሄራዊ ቡድን ደረጃ የወከለው ከማል ለኢትዮጵያ የመጫወት ፍላጎት እንዳላው በጥቅምት ወር ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፁ ይታወሳል፡፡

ያጋሩ