መቐለ 70 እንደርታ ከወጋገን ባንክ የአጋርነት ውል ፈፀመ

ባለፈው ዓመት መጀመርያ ከራያ ቢራ ጋር ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የማሊያ ማስታወቂያ ውል ያሰሩት መቐለዎች አሁን ደግሞ ከወጋገን ባንክ ጋር አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል።

ዛሬ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ የሆነው ይህ ስምምነት ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ስምምነቱም ለመቐለ 8 ሚልዮን የሚያስገኝ ይሆናል። ክለቡም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እና ዝግጅቶች ላይ ድርጅቱን የሚያስተዋውቅ ይሆናል።

በከሰተ ለገሰ (ዶ/ር)፣ አቶ ሽፈራው ተ\ኃይማኖት እና በወጋገን ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደሳለኝ እምብዛ በጋራ ዛሬ የተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫው በሁለቱም አካላት በርካታ ሃሳቦች የተነሱበት ነበር።

ቀድመው ሃሳባቸው የሰጡት ከሰተ ለገሰ (ዶ/ር) ሲሆኑ አዲሱ ውል የክለባቸው ገቢ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀው ከወጋገን ባንክ ጋር አብረው በመስራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል። ” ክለባችን በአብዛኛው በድጎማ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው ፤ ቡድኑም ለወደፊት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ይፈለጋል። ከድጎማው ለመውጣትም ከመንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አብሮ በመስራት ክለቡ ራሱ እንዲችል መስራት አስፈላጊ ነው ” ብለዋል።

በመቀጠል ሃሳባቸው የሰጡት አቶ ሽፈራው ተ/ኃይማኖት ሲሆኑ ስምምነቱ ለወደፊት የክለባቸው ህልውና ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል። ” ከባንኩ ጋር የምናደርገው ስምምነት ከሌላ ስምምነቶች የተለየ ነው፤ ስምንት ሚልዮን ከወጪያችን አንፃር ትልቅ ብለን አናስበውም። ከባንኩ የምንጠብቀው ብዙ ነገር አለ። ከጊዜ በኃላ ክለባችንን ወደ ንግድ ተቋምነት እንቀይረዋለን። የዛኔም ከአንዳቸው ባንኮች ጋር እንሰራለን፤ አሁን ግን ከግል ባንኮች ትልቁ እና አንጋፋውን መርጠናል። ለስምንት ሚልዮን ብቻ አይደለም የመረጥናቸው። ለሌሎች ትላልቅ የንግድ እንቅስቃሴዎችም ጭምር ነው። ከግዜ በኃላ ከባንኮች በመቶዎች የሚጠጉ ሚልዮኖች መበደራችን አይቀርም። የተደረሰው ስምምነትም ይሄ ነው። ከብሩ ባሻገር የንግድ ስራዎች ማማከርም አንዱ የስምምነት አካል ነው” ብለዋል።

በመጨረሻ ላይ ሃሳባቸው የሰጡት የወጋገን ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ደሳለኝ እምብዛ ናቸው። “ባንካችን በኢትዮጵያ በጣም ሰፋፊ ስራዎች እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው። ከመቐለ ጋር የምናደርገው ስምምነት የማስታወቅያ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ነው ፤ ክለቡ ባለፈው ዓመት እንዳስመዘገበው ጥሩ ውጤት በቀጣይ የውድድር ዓመትም ለማስቀጠል ማሕበራዊ መሰረቱ እና ተደራሽነቱን ማስፋት የግድ ነው። ለዚህ አስተዋፅኦ ለማድረግም ስምምነታችን በማስታወቅያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ክለቡ በሚጀምረው ስራ እኛ የገንዘብ አገልግሎት እንሰጣለን” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ