ባለፈው የውድድር ዓመት ለከፍተኛ ሊጉ አክሱም ከተማ የአንድ ዓመት ውል ፈርሞ የውል ጊዜው ሳይጠናቀቅ ከቡድኑ ጋር የተለያየው የተከላካይ ክፍል ተጫዋች መብራህቱ ኃይለሥላሴ ከቡድኑ ጋር የተለያየሁበት መንገድ አግባብ አይደለም በማለት ለፌደሬሽኑ ቅሬታውን መግለፁ ይታወሳል። ዲሲፕሊን ኮሚቴው “አክሱም ከተማ ቀሪ የስድስት ወር ውል እያለብኝ አለአግባብ ከቡድኑ መሰናበቴን በመግለፅ የቀሪ ወራት ደሞዜ እንዲከፍለኝ የካቲት 16/2011 ወስኖልኛል።” የሚለው ተጫዋቹ ጉዳዩ በመጓተቱ ብዙ መጉላላቶች እንደደረሱበት ተናግሯል።
የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉም ኮሚቴው ከወር በፊት አክሱም ከተማ ከፌደሬሽኑ ግልጋሎት እንዳያገኝ ቢያግደው ተጫዋቹ የተወሰነብኝ ውሳኔ በጊዜው አላለቀም ብሎ ቅሬታውን ገልጿል። “እኔ የዲስፕሊን ኮሚቴ የወሰነብኝ ውሳኔ ቶሎ እንዲያልቅልኝ ነው የምፈልገው፤ ጉዳዩ ስድስት ወር ገደማ ሆኖታል። ሆኖም እስካሁን ማለቅ አልቻለም። እኔም በሱ ምክንያት በመጉላላት ላይ ነኝ ” ብሏል።
ጉዳዩን አስመልክተን ያናገርናቸው የአክሱም ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ክንፈ ይልማ ችግሩ የቡድኑ እንዳልሆነ ተናግረዋል። “ቡድኑ በተደጋጋሚ ጠርቶት የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ በቦታው መገኘት አልቻለም። አክሱም ከተማ በጣም ይፈልገው ነበር። በሱ ቦታ እንደውም ቡድን ክፍት ነበር። የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ለኛ ነው የተወሰነልን። የታገደው ቡድናችን ሳይሆን ተጫዋቹ ነው። ” ብለዋል።
የዲስፕሊን ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ የሰጣቸው ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው 👇
© ሶከር ኢትዮጵያ