ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት አጥቂዎችን የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት አስፈርሟል

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ሀዲያ ሆሳዕና በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ሰዓታት ተጨማሪ ሁለት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች አስፈርመዋል። መሀመድ ናስር እና ቢስማርክ አፖንግም አዲሶቹ ፈራሚዎች ናቸው።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሲዳማ ቡና ያሳለፈው መሐመድ ናስር ባለፉት 12 ዓመታት በተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ አጥቂ ነው። ኤሌክትሪክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዳማ ከተማ፣ መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ጅማ አባ ቡና እና ፋሲል ከነማ የመሳሰሉ ክለቦች የተጫወተው መሐመድ ዝውውሩ ለክለቡ የአጥቂ መስመር ልምድን የሚጨምር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ የቀድሞው የመቀለ 70 እንደርታ እንዲሁም ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በቅርቡ ሌላኛው ክለቡን ከተቀላቀለው ቢስማርክ አፒያና ሳሊፍ ፎፋና ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ሽረ በሊጉ እንዲቆይ ከፍተኛ ሚና መጫወት የቻለው ጋናዊዉ ቢስማርክ ኦፖንግ ነው። በመስመር እና መሐል አጥቂነት የሚጫወተው ቢስማርክ ለመጀመርያ ተሰላፊነት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ፉክክር ያደርጋል።

በክረምቱ በአንፃራዊነት የቡድኑን ጥራት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ዝውውሮችን የፈፀሙት ሆሳዕናዎች በቅርቡ የሴራሊዮናዊዉን አጥቂ ሙሳ ካማራን እንዲሁም ቢስማርክ አፒያን የአጥቂ መስመራቸውን ለማጠናከር ያስፈረሙ ሲሆን በአዳማ ከተማ በሚካሄደው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ