ቻን 2020| የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሩዋንዳው ጨዋታ ዙርያ ካፍን ማብራሪያ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በፊት በ2020 የቻን ማጣርያ በሩዋንዳ በድምር ውጤት ተሸነፎ ከውድድር መውጣቱ ሲታወስ ኢትዮጵያም ሩዋንዳ በመጀመርያው የመቐለ ጨዋታ ላይ የስብስቡ አካል በነበረ ተጫዋች ተገቢነት ዙሪያ ላይ ካፍ ማብራሪያ እንዲሰጣት መጠየቋ ታውቋል።

በሁለተኛ ዙር የቻን ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ሩዋንዳን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ኤሪክ ሩታንጋ የተሰኘው የሩዋንዳ ተጫዋች ፓስፖርት ላይ አሻሚ የሆነ የትውልድ ዘመን ስለተገኘ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣት ለካፍ ጥያቄ አስገብታለች።

ሩታንጋ ከዚህ ቀደም ለሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች ሲጫወት በፓስፖርቱ ላይ የተጠቀሰው የትውልድ ዘመን እና በአሁኑ የቻን ማጣሪያ ላይ ባስመዘገበው የትውልድ ዘመን ላይ ልዩነቶች ስለመኖራቸው የኢትዮጵያ የማብራሪያ ጥያቄ እንደሚያትትም ለማወቅ ተችሏል። የማብራሪያው መነሻ የሆነውም የቻን የውድድር ደንብ በተጫዋቾች መረጃዎች ላይ የተቀመጠውን አንቀጽ የሚጻረር በመሆኑ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

በጉዳዩ ዙርያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚመለከታቸው አካላት መረጃ እና ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በተያያዘ የዋልያዎቹ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወርሃዊ የፊፋ የሀገራት ደረጃ ላይ ባሳለፍነው ወር በነበረበት 151ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ