ከፍተኛ ሊግ፡ አአ ፖሊስ መሪነቱን ሲያስረክብ አአ ከተማ እና ወልድያ በአሸናፊነታቸው ቀጥለዋል

 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ተካሂደዋል፡፡ በተካሄዱ 15 ጨዋታዎችም የደረጃ ሰንጠረዦች ላይ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ወልድያ እና አዲስ አበባ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በማሸነፍ አጀማመራቸውን ሲያሳምሩ ጅማ ከተማ እና አአ ፖሊስ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል፡፡

ምድብ ሀ

መልካ ቆሌ ላይ ወልዋሎን ያስተናገደው ወልድያ 1-0 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ለብቻው ተቆናጧል፡፡ የወልድያን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው እዮብ ወልደማርያም ነው፡፡ ወልድያ መድን እና ቡራዩ ከተማን ሲያሸንፍ ግቦች ያስቆጠረው እዮብ ዛሬም የቡድኑን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ አሳረፎ የወሎውን ቡድን ለድል አብቅቷል፡፡ ወልድያ ያደረጋቸውን 4 ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ የምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥን ለብቻው መምራት ጀምሯል፡፡

የምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥን በግብ ልዩነት እየመራ ወደ ኮምቦልቻ ያቀናው አዲስ አበባ ፖሊስ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የኮምቦልቻን የድል ግብ ናሂል መሃመድ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎም ወሎ ኮምቦልቻ ደረጃውን ወደ 4ኛ አሻሽሏል፡፡

ትግራይ ስታድየም ላይ አማራ ውሃ ስራን ያስተናገደው መቐለ ከተማ በኸይረዲን ፣ ሀብታሙ እና ቢንያም ግቦች 3-1 አሸንፏል፡፡ ደረጃውንም ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል፡፡ የአማራ ውሃ ስራን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈው የመስመር አማካዩ ጅላሎ ሻፊ ነው፡፡

ወደ ባህርዳር ያቀናው ቡራዩ ከተማ ባህርዳር ከተማን አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ባህርዳር ከተማ በተዘራ ጌታቸው ግብ 1-0 ሲመራ ቢቆይም ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ሙከረም ሃለቱ እና ሰለሞን ረዳ ግብ አስቆጥረው ቡራዩ ከተማን ለድል አብቅተዋል፡፡

አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ሱሉልታ ከተማን አስተናግዶ 21 አሸንፏል፡፡ የሙገርን የድል ግቦች አሸናፊ ከበደ እና ሱራፌል ጌታቸው ከመረብ ሲሳርፉ ዳንኤል ፀጋዬ የሱሉልታን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ወደ አክሱም የተጓዘው ኢትዮጵያ መድን የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አሳክቷል፡፡ መድን አክሱምን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ አብዱልናስር ፈቱዲን እና አስራት ሸገሬ የሰማያዊዎቹን የድል ግብ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ትላንት በተደረገ አንድ ጨዋታ አበበ ቢቂላ ላይ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት በአስደናቂ እንቅስቃሴ ፋሲል ከተማን 3-2 አሸንፏል፡፡ የውሃ ስፖርትን የድል ግብ አስጨናቂ ተስፋዬ ፣ ኄኖክ ታደሰ እና ለታ ዋቅጋሪ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የፋሲል ከተማን ግቦች ኄኖክ ገምቴሳ በአወዛጋቢ ቅጣት ምት እና ከድር ኸይረዲን በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል፡፡ በዘንድሮ ውድድር ዘመን ማራኪ እግርኳስን እየተጫወተ የሚገኘው ውሃ ስፖርት ያስቆጠሯቸው ግቦች አስደናቂ ነበሩ፡፡ በተለይም ኄኖክ የግብ ጠባቂውን በተከላካዮች መጋረድ ተመልክቶ ያስቆጠረው ግብ እና ከበርካታ ማራኪ ቅብብሎች በኋላ በለታ ዋቅጋሪ የተቆጠረችው ግብ በስፍራው የተገኘውን ተመልካች አስደንቋል፡፡

በዚሁ ምድብ ሰሜንሸዋ ደብረብርሃን ከ ሰበታ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ አፄ ዘርዓያዕቆብ ስታድየም ለባዛር ፕሮግራም በመያዙ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡

-የምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

G A

ምድብ ለ

አዲስ አበባ ከተማ አሁንም በአሸናፊነት ቀጥሏል፡፡ በአበበ ቢቂላ ከ ፌዴራል ፖሊስ ጋር ባደረገው ጨዋታም ከሙሉ የጨዋታ ብልቻ ጋር 2-1 አሸንፏል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን የድል ግብ የፌዴራል ፖሊሱ ክብሮም እሸቱ በራሱ ግብ ላይ እንዲሁም የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ኮከብ ዮናታን ብርሃኔ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ብቸኛ ግብ ቻላቸው ቤዛ አስቆጥሯል፡፡

ሻሸመኔ ከተማ አርሲ ነገሌን 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 2ኛ ከፍ አድርጓል፡፡ የሻሸመኔን የድል ግቦች ፀጋ ጎሳዬ እና ብርሃኑ በቀለ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ወደ ጅማ ያቀናው ሀላባ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡ አበበ ታደሰ የበርበሬዎቹን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጅማ ከተማም በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

ወራቤ ላይ ወራቤ ከተማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል፡፡ የወራቤን የድል ግቦች አለማየሁ ሽብሩ ፣ ፈቱረሂም ሲቾ እና ፈድሉ ሃምዛ አስቆጥረዋል፡፡

ጂንካ ላይ ጂንካ ከተማ ባቱን 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ ተስፋሁን ተሰማ ፣ ሚልዮን መንገሻ እና ብሩክ ብርሃኑ የጂንካን የማሸነፍያ ግቦች ከመረብ ሲያሳርፉ ሱራፌል አየለ የባቱ ከተማን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ወደ ነቀምት ያቀናው ናሽናል ሴሜንት ካለ ግብ አቻ ሲለያይ ነገሌ ቦረናን ያስተናገደው ድሬዳዋ ፖሊስ ነገሌ ቦረናን 2-0 አሸንፈዋል፡፡ የድሬዳዋ ፖሊስን የድል ግብ አፈወርቅ ኃይሌ እና ዮርዳኖስ አባይ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የቀድሞው የብሄራዊ ቡድን እና የኤሌክትሪክ ታላቅ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ በሃገሪቱ ሶስት የሊግ እርከኖች (ፕሪሚየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ) ግ ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡

ትላንት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ወደ ሀዋሳ ያቀናው ጅማ አባቡና ደቡብ ፖሊስን 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ተመስገን ለገሰ እና ዳዊት ተፈራ የአባቡናን የድል ግብ ከመረብ ሲሳርፉ ምስጋናው ወልደዮሃንስ የደቡብ ፖሊስን ግብ አስቆጥሯል፡፡ በጨዋታው ለጅማ አባቡና ድል ከፍተኛውን ሚና የተወጣው ዳዊት ተፈራ ከተመልካች አድናቆት አግኝቷል፡፡

ከ4 ሳምንታት ጨዋታዎች በኋላ የምድብ ለ የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡-

gggggggggggggggg

 

ያጋሩ