ያለፉትን ዓመታት የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በመባል ሲጠራ የቆየው ውድድር የሥያሜ ለውጥ በማድረግ የደቡብ ሠላም ዋንጫ በሚል የሚጠራ ሲሆን ነገ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርአትም ይደረጋል፡፡
ከጥቅምት 20 እስከ ህዳር 1 ድረስ በሀዋሳ የሚደረገው ይህ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን በካስቴል ስያሜ ለአምስተኛ ጊዜ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም ስያሜው ተለውጦ ደቡብ የሠላም ዋንጫ በሚል ይጠራል፡፡ ሊለወጥ የቻለበት ምክንያት ደግሞ የክለቦችን ግንኙነት ሠላማዊ ለማድረግ እና ከእግር ኳስ ውጪ ሌሎች የሚንፀባረቁ እግር ኳሳዊ ያልሆኑ ነገሮች እንዳይኖሩ በማሰብ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ነገ በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ቀን 10:00 የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርአትም ይከወናል፡፡
በክልሉ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ወላይታ ድቻ፣ ሀዲያ ሆሳዕናን ከፕሪምየር ሊጉ የሚያካትት ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ በፎርማት ለውጥ ምክንያት አድጋችዋል ተብለው የነበሩትና በከፍተኛ ሊጉ የሚወዳደሩት አርባምንጭ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስን ጨምሮ በተጋዥነት መቐለ 70እንደርታ እና የአዳማ ሲቲ ካፕ ላይደረግ የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩ አዳማ ከተማም ተካፋይ ሊሆን እንደሚችል አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
ውድድሩን ካለፉት ዓመታት ለየት ባለ መልኩ ለማዘጋጀት የታቀደ ሲሆን በየጨወታው ጥሩ እንቅስቃሴን ላደረጉ ተጫዋቾች (የጨዋታው ኮከብ) ሽልማት እንዲሁም አሸናፊ ለሆኑ ክለቦች እና ተሳታፊዎች የገንዘብ ሽልማቶች እንደሚበረከት ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ