የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ረዳቶች ታውቀዋል

የሉሲዎቹ አሰልጣኝ በመሆን የተሾሙት አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው መሠረት ማኒን ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ ሲመርጡ ሽመልስ ጥላሁን ደግሞ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ሾመዋል።

የሴካፋ የሴቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣዩ ወር የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የንግድ ባንክ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን በሦስት ወራት ኮንትራት መሾሙ ይታወሳል፡፡ አሰልጣኙ ለነኚህ ውድድሮች 23 ያህል ተጫዋቾችን የመረጡ ሲሆን ረዳቶቻቸውንም ዛሬ አሳውቀዋል።

አሰልጣኝ ብርሀኑ አስቀድሞ የቀድሞው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እና የአሁኑ የቡታጅራ አሰልጣኝ አስራት አባተን በረዳት አሰልጣኝነት ለመቅጠር ፍላጎት ቢኖራቸውም አሰልጣኙ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ለዋና አሰልጣኝነት ስትፎካከር የነበረችው አሰልጣኝ መሠረት ማኔን በረዳት አሰልጣኝነት እንድትሰራ ተመርጣለች ፡፡ የቀደሞዋ የድሬዳዋ ከተማ ወንዶች እና የሴት ቡድን አሰልጣኝ መሠረት ከዚህ ቀደም ብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት የሴካፋ ውድድር ላይ የተሳተፈች ሲሆን በ2011 የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ቡድንን በአሰልጣኝነት መርታለች፡፡ ከመዲናው ክለብ ጋር ከተለያየች በኋላ ከሰሞኑ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ተደርጋ የተሾመች ሲሆን አሁን ደግሞ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ረዳት ተደርጋ ተመርጣለች፡፡

የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ሽመልስ ጥላሁን ተሹሟል፡፡ የአዲስ አበባ እና የጉለሌ ክፍለ ከተማን በዋና እና በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ከዚህ በፊት ያገለገው አሰልጣኙ ዘንድሮ ደግሞ የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ የተቀጠረ ሲሆን የሉሲዎቹ የአሰልጣኝ ቡድን አባል በመሆን ተቀላቅሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ