ከስምንት ዓመታት በኃላ በድጋሚ የሚደረገው የአዳማ ከተማ ዋንጫ የፊታችን ሀሙስ የሚጀመር ሲሆን በነገው ዕለትም የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ይከወናል፡፡
በአዳማ ከተማ ስፖርት ክለብ አስተናጋጅነት ይደረጋል የተባለው ይህ ውድድር ጥቅምት 20 በስምንት ክለቦች መካከል ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በከተማዋ በነበረው ያለ መረጋጋት ቀኑ ወደ ጥቅምት 27 ሀሙስ ተለውጦ የሚጀመር መሆኑን የአዳማ ከተማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስፈፃሚ እና ፀሀፊ አቶ አህመድ ሁሴን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡
2005 ውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ ሲደረግ ሀዋሳ ከተማ ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ ያለፉትን ስምንት ዓመታት ሳይደረግ ከቆየ በኃላ ዘንድሮ በድጋሚ ጅማሮውን ሲያደርግ አስቀድሞ ይሳተፋሉ ከተባለው ቁጥር በሁለት ቀንሶ በስድስት ክለቦች መካከል ለአስር ተከታታይ ቀናት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እየተደረገ ይቀጥላል፡፡ ነገ ሰኞ 8:00 ሰአት የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት የሚደረግ ሲሆን ተሳታፊ ክለቦችም ተለይተው ታውቀዋል፡፡ አዘጋጁ አዳማ ከተማን ጨምሮ ጅማ አባጅፋር፣ ፋሲል ከነማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ለመሳለፍ ማረጋገጫ የሰጡ ስድስት ክለቦችም መሆናቸው አቶ አህመድ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ