ከፍተኛ ሊግ | ነገሌ አርሲ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሊግ “ምድብ ለ” በመጨረሻው ሳምንት በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡት አርሲ ነገሊ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተሻለ መልኩ ለመቅረብ የአስራአንድ ተጫዋቾች ዝውውር ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በግብጠባቂ ስፍራ ሁለት ተጫዋቾች ፈርመዋል ፤ የቀድሞው ወልቂጤ ከተማ ኒያላ እና ሀረር ሲቲ ግብጠባቂ ብርሃኑ ወልደማርያም እንዲሁም ምንተስኖት ኃይሌ ከአንደኛ ሊግ ተሳታፊው ላስታ ላሊበላ ሌላኛው ቡድኑን የተቀላቀለ ግብጠባቂ ነው፡፡

ደካማ የነበረውን የተከላካይ መስመራቸውን ለማጠናከር የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል። የቀኝ መስመር ተከላካዩ ያያ አሎ ከሀምበሪቾ ሲፈርም መሀል ተከላካዮቹ ታዬ ገሹ ከአዳማ ተስፋ ቡድን፣ ማንያዘዋል በላቸው ከባሌ ሮቤ እንዲሁም በኃይሉ ተስፋዬን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ማስፈረም ችለዋል። ከአዳማ ተስፋ ቡድን ቡድኑን የተቀላቀለው ታዬ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት እንደነበረም ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም በአጥቂ ስፍራ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳን ከአዳማ ተስፋ ቡድን፣ ሙሉቀን ተሾመ ከሻሸመኔ ከተማ ፤ በደደቢት ተስፋ ቡድን መጫወት የቻለው አሸብር ኦቶራ ከነገሌ ቦረና፤ በባሌ ሮቤና ሀሰን ሁሴንና በኢኮስኮ ተስፋ ሰጪ ቆይታ የነበረው ሚካኤል ወልደሩፋኤል ከሀምበሪቾ በአዲስ መልኩ እየዋቀረ የሚገኘውን የአርሲ ነገሌ በአጥቂ ስፍራ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜና የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋች እና አንበል የነበረው ሀሰን በሽር በምክትል አሰልጣኝነት ቡድኑን እንዲያገለግል ተሹሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ