የ2011 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ኮከቦች ሽልማት እጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ መልክ ያካሄደው የኮከቦች ሽልማት ዘንድሮ እስካሁን የመካሄድ ያለመካሄዱ ጉዳይ አለየለትም፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በስሩ የሚያከናውናቸው የተለያዩ ውድድሮች ላይ የተሻለ የውድድር ዘመን ላሳለፉ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች በተነጣጠለ መልኩ ይከናወን የነበረውን ሽልማት በማስቀረት ወጥነት ባለው መልኩ በአንድ ቦታ ላይ የሽልማት መርሃግብርን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ነገርግን የ2011 የውድድር ዘመን ምርጦች ሽልማት የመካሄዱ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልፀዋል ፤ ምንጮቹ አያይዘውም በከፍተኛ የስራ መደራረብ የተነሳ ጉዳዩ ሳይዘነጋ እንዳልቀረም ገልፀዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙርያ ምላሽን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ብታደርግም ምላሽ ማግኘት ሳትችል ቀርታለች ፤ በጉዳዩ ቅር የተሰኙ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፌደሬሽኑ ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ላይ በኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ በየክለባቸው የተሻለ ብቃት ያሳዩ ያላቸውን ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ይፋ በማድረግ በአጭር የፅሁፍ መልእክት ድምፅ በማሰባሰብ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዙር ኮከብ ተጫዋቾችን ለመሸለም እንቅስቃሴ ቢጀምርም ፤ ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅት ወደ ትግበራ የገባው አካሄድ ስኬታማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ