የመቐለ 70 እንደርታው ግብ ጠባቂ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሀገሩ ጥሪ ደርሶታል

ላለፉት ሁለት ዓመታት መቐለን በቋሚነት ያገለገለው የኢኳቶሪያል ጊንያዊ ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ሃገሩ ከታንዛንያ እና ሊቢያ ለምታደርጋቸው ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ጥሪ ደርሶታል።

በክረምቱ ዝውውር መስኮት ስሙ ከበርካታ ክለቦች ሲያያዝ ከቆየ በኃላ በመጨረሻው ሰዓት ከቻምፒዮኖቹ ጋር ለመቆየት ፊርማውን ያኖረው ግብ ጠባቂው ላለፉት ሥስት ዓመታት በተለያዩ የማጣርያ ጨዋታዎች ሃገሩን በቋሚነት ማገልገሉ ይታወቃል።

የቡድኑ ሁለተኛ አምበል የሆነውና በበርካታ ጨዋታዎች ቡድኑን በአምበልነት ለመምራት ዕድል ያገኘው ግብ ጠባቂው ከዚህ በፊት በሁለት አፍሪካ ዋንጫዎች መሳተፉ ሲታወስ አሁንም ለካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ከቱኒዝያ፣ ሊቢያ እና ታንዛንያ የተደለደለችው ሀገሩን ወደ ውድድሩ ለመመለስ በማለም ማጣርያውን ለመጀመር ወደ ስፍራው ያቀናል።

በተያያዘ ዜና ኔዘርላንዳዊው የቀድሞ የካሜሩን አሰልጣኝ ክላረንስ ሲዶርፍ አሰልጣኝ አድርገው ለመቅጠር ተቃርበው የነበሩት ኢኳቶርያል ጊኒዎች ከሰዓታት በፊት የቀድሞ የኬንያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ሰባስትያን ሚኜን አሰልጣኝ አድርገው ቀጥረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ