የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ባደረገው ስብሰባ የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በኅዳር ወር መጨረሻ እንዲጀምር ወስኗል።
በቅርቡ የሊጉ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አሊሚራህ መሐመድ በመሩት ስብሰባ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የማርኬቲንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን በውድድሩ ዙርያም ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ መነሻነት ውድድሩን አስመልክቶ ውሳኔዎች የተላለፉ ሲሆን የክለቦች ምዝገባ ኅዳር 8፣ ለዳኞች እና ኮሚሽነሮች የክለቦች ክፍያ ደግሞ ኅዳር 15 ድረስ እንዲጠናቀቅ ተወስኗል፡፡ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱ ኅዳር 20 ከተካሄደ ከአንድ ሳምንት በኋላም ኅዳር 27 ውድድሩ ይጀመራል ተብሏል፡፡
በጉዳዩ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
” እንደሚታወቀው ውድድሩ ከፍተኛ ውጥረት አለበት፤ ይህን ውድድር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ ነው የዘንድሮው የውድድር ዘመን ዋነኛ እቅዳችን፡፡ ስፖርታዊ ጨዋነት ማስፈን ላይ ቅድሚያ በመስጠት እንሰራለን፡፡ ከወዲሁ ክለቦች ሊያውቁ የሚገባው ማንኛውንም የውድድር ስፍራ ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ቢከሰቱ ምንም አይነት ማስተባባያ የማንቀበል መሆኑን ነው፡፡
“በተመሳሳይ በዘንድሮ ዓመት በትይዩ የምንሰራው የሜዳዎችን ጥራት የማሻሻል ተግባርን ነው፡፡ የተጫዋቾችን ብቃት ማሻሻል እንዲሁም እግር ኳሳዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው የሚሰሩ ስራዎች እንዲሁ ዘንድሮ በጥልቀት የምንሰራ ይሆናል። በአጠቃላይ እግርኳሱ የሰላምና የፍቅር መድረክ እንዲሆን የበኩላችንን እንሰራለን፡፡”
© ሶከር ኢትዮጵያ