አዳማ ዋንጫ | አዳማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

Read Time:1 Minute, 16 Second

በአዳማ ከተማ ዋንጫ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን በአዲስ አዳጊው ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሜዳው አማካይ ክፍል ላይ ባመዘነው ጨዋታ ጅማሮ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ሲቸገሩ ተስተውሏል። ብዙ ሙከራ ባልታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የአዳማው ዱላ ሙላቱ በ5ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ቀጥታ ወደ ቀኝ የገለበጠው ኳስ ተስፋዬ ነጋሽ በአግባቡ በመቆጣጠር እየገፋ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ አዳማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በጨዋታው እምብዛም የግብ ዕድል ሲፈጠር ባይታይም ዱላ ሙላቱ በ18 ኛው ደቂቃ ከመሀል በተሻገረ ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብነት ለወጠው ቢባልም ታሪክ ጌትነት አድኖበታል። በቶሎ ወደ ሆሳዕናዎች ግብ ክልል ለመድረስ ሙከራ የሚደርጉት አዳማዎች በቀኝ መስመር ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም እምብዛም አደጋ መፍጠር ያልቻሉበት አጋማሽ ነበር። በተመሳሳይ ሆሳዕናዎችም በመጀመሪያው አጋማሽ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ነበር ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ያመሩት።


በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከመጀመሪያው ፍፁም የተለዩ ሆነው ቀርበዋል። አጋማሹ እንደጀመረ በሄኖክ አርፍጮ ፣ በእዩኤል ሳሙኤል እና በቢስማርክ ኦፖንግ አማካይነት ጠንካራ ሙከራዎች በማድረግ ባለሜዳዎቹን በተደጋጋሚ መፈተን ችለዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይም በእዩኤል ሳሙኤል ላይ በተፈፀመ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አርፍጮ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። ከግቡ በኋላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉት ነብሮቹ እምብዛም ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል በመግባት ለማጥቃት ሲሞክሩ አልታዩም።

በአንፃሩ አዳማዎች የአሸናፊነት ግብ ፍለጋ ወደ ፊት ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም የጨዋታውን ውጤት ሳይቀይሩ ቀርተዋል። በተለይም በ78ኛው ደቂቃ ከታሪክ የተመለሰውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አዲስ ህንፃ ወደ ግብነት ለወጠው ሲባል ታሪክ ከወደቀበት ተነስቶ የመለሰበት እንዲሁም በጨዋታው ለሆሳዕናዎች ፈተና ሆኖ ያመሸው የተስፋዬ ነጋሽ ሁለት የግብ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው ያለተጨማሪ ግቦች በ 1-1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!