አአ ከተማ ዋንጫ| ቅዱስ ጊዮርጊስ በመከላከያ ሽንፈት አስተናገደ

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመከላከያ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናገደ፡፡

በርከት ያሉ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ያስጀመሩት ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ጅማሮውን ባደረገው ጨዋታ በክረምቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል አቤል እንዳለ እና ኤቱሳይ ኤንዶን በመጀመሪያ 11 ውስጥ በማካተት የጀመሩት ጊዮርጊሶች ሰልሀዲን ሰኢድ በተመሳሳይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ አሰልፈዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሶች መጠነኛ የበላይነት በታበየበት የቡድኖቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ጊዮርጊሶች በተሻለ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ በተለይም ከርቀት የተደረጉ ሙከራዎች ጊዮርጊሶች ለግብ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ወደ ጊዮርጊስ የሜዳ አጋማሽ ለመድረስ ተቸግረው የተስተዋሉት መከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ከቅጣት ምት ያሻሙትን ኳስ የጊዮርጊሱ ተከላካይ ሜንሱ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ሳይጠበቅ የመጀመሪያ አጋማሽን በመሪነት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በግቧ የተነቃቁ የሚመስሉት መከላከያዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች እጅግ ማራኪ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ለተመልካች ማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህም በ47ኛው ደቂቃ በግሩም መልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

በሂደት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ጊዮርጊሶች በ65ኛው ደቂቃ ሰልሀዲን ሰኢድን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የክለቡ አዲስ ፈራሚ አጥቂ ዛቦ ቴግዊ በመጀመሪያ የኳስ ንክኪው የግብ ልዩነት ወደ አንድ ያጠበበች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል ፤ በዚህም መከላከያ ሳይጠበቅ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ቴዎድሮስ ታፈሰ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ