በአዳማ ከተማ ዋንጫ የዛሬ ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 መርታት ችሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ 20 ደቂቃዎች ጥሩ የተንቀሳቀሱት ድሬዎች ወደ ፋሲል የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ የሚደርጉት ጥረት ግብ ባይገኝበትም ጥሩ የሚባል ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ምት የገቡት ፋሲሎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ ችለዋል። ሆኖም በተደጋጋሚ በነጻ አቋቋም ዕድሎችን ሲያገኙ የነበሩት የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ደካማ ውሳኔ ጥረቶቻቸው ፍሬያማ እንዳይሆኑ አድርጓል። በዚህም 33ኛው እና 35ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብሎች የተገኙትን ኳስች ኦሴይ ማውሊ እና ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብነት ሳይቀይሯቸው ቀርተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለግብ የተጠናቀቀ ሆኗል።
ከዕረፍት መልስ ፋሲሎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫዎት እንዲሁም ድሬዳዎች በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በግራ መስመር የተጫወተው የፋሲሉ አጥቂ ማውሊ ለድሬዳዋ ተከላካይ ክፍል የራስ ምታት ሆኖ ባመሸበት ሁለተኛ አጋማሽ 52ኛው ደቂቃ ያሻማውን ኳስ ሽመክት ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በመልሶ ማጥቃት በሚወጡት ድሬዳዎች በኩልም በ48ኛው ደቂቃ የሳሙኤል ዘሪሁን የግንባር ኳስ በሳማኬ ሲድንበት በሌላ አጋጣሚ ኳሶ እየገፋ በመሄድ የሳማኬን አቋቋም በማየት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ ለድሬዳዎች እጅጉን የሚያስቆጩ ነበሩ።
የፋሲሎች አዲሱ ፈራሚ ኦሰይ ማውሊ በ63ኛው ደቂቃ በግምት 25 ሜትር ላይ የመታትን ኳስ ወደ ግብነት በመለወጥ አፄዎቹን ቀዳሚ ሲያደርግ ከግቧ መገኘት በኃላ ይበልጥ የተነቃቁ የሚመስሉት ፋሲሎች ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። በ82ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል የተሻገረውን ኳስም ሙጂብ ቃሲም በሚገርም ሁኔታ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ሊያደርገው ችሏል። ከግቦቹ በተጨማሪ 76ኛው ደቂቃ ላይ አማረ በቀለ በሽመክት ጉግሳ ጥፋት ተሰርቶበት እንዲወጣ የሆነባቸው ድሬዎች ውጤቱን ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በዛው ተጠናቋል።
ጨዋታው በፋሲሎች የ2-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ምድቡን በስድስት ነጥብና በአራት ንፁህ ግቦች እየመራ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ