የትግራይ ዋንጫ ሁለተኛ መርሃግብር የነበረውና በመቐለ እና በወላይታ ድቻ መካከል የተደረገው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት የግብ ዕድሎች በታየበት ጨዋታ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት መቐለዎች ነበሩ። ኤፍሬም አሻሞ ያሬድ ከበደ ከመስመር ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር።
በመስመሮች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እና በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መቐለዎች ከላይ ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ዮናስ ገረመው እና ኦኪኪ ኦፎላቢ አንድ ሁለት ተቀባብለው ኦኪኪ አክርሮ መቶ ወንድወሰን አሸናፊ ያዳነው እና ኤፍሬም አሻሞ ከመስመር አሻግሮት ኦኪኪ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው።
በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ወላይታ ድቻዎችም በቁጥር ቀላል የማይባሉ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ባየ ገዛኸኝ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶት ሶፈንያስ ሰይፈ ያዳነው እና እንድሪስ ሰይድ አሻምቶት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡት ኳስ ይጠቀሳል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት እና በተወሰነ መልኩ የመቐለ ብልጫ በታየበት ጨዋታ በተለይም በምዓም አናስስት በኩል በርካታ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። ከነዚህም ዮናስ ገረመው በጥሩ ሁኔታ አታሎ ገብቶ ያልተጠቀመበት ዕድል ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ከኦኪኪ ኦፎላቢ የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ዳንኤል ደምሴ በግምባር ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩት ጦና ንቦችም በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል፤ በተለይም ባየ ገዛኸኝ ከሶፈንያስ ሰይፈ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት ኳስ እጅግ በጣም አስቆጪ ነበር።
ውጤቱ በአቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች አክሱም ከተማን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የጨዋታው ኮከብም የመቐለው ተከላካይ ላውረንስ ኤድዋርዶ ሆኖ ተመርጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ