ትግራይ ዋንጫ | ስሑል ሽረ እና ሶሎዳ ዓድዋ ነጥብ ተጋርተዋል

የትግራይ ዋንጫ ዛሬም በአንድ ጨዋታ ሲቀጥል በምድብ ሁለት የሚገኙትን ስሑል ሽረ እና ሶሎዳ ዓድዋን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጥቂት የግብ ዕድሎች እና ብዙም ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ስሑል ሽረዎች ናቸው።
ዓብዱሰላም አማን ከመስመር አሻምቷት ሳሊፍ ፎፋና በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ሙከራም የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነች። በቀኝ መስመር አዘንብለው ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት ሽረዎች ከተጠቀሰው መስመር በተነሱት ተሻጋሪ ኳሶች ሁለት የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። በተለይም ዲድዬ ለብሪ ከአብዱሰላም አማን የተሻገረለትን ኳስ መትቶ ሰንደይ ሮትሚ ያወጣት ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች። መድሃኔ ብርሃኔ ከመስመር አሻምቶ ሳሊፍ ፎፋና ብቻው ከሰንደይ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስም ሌላ የምትጠቀስ ሙከራ ነች።

በጨዋታው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ሶሎዳ ዓድዋዎችም ምንም እንኳ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎች አድርገዋል። ሙሉዓለም በየነ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ እና መሐሪ አድሐኖም ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። ሙሉዓለም በየነ አክርሮ መቶ ወንድወሰን አሸናፊ በጥሩ ሁኔታ ያወጣው ሙከራም ለግብ የቀረበ ነበር።

ከመጀመርያ አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴዎ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ስሑል ሽረዎች ተሽለው ከታዩበት ነበር። ሃብታሙ ሽዋለም አክርሮ መቶት ሰንደይ ሮትሚ በመለሰው ኳስ ጥቃታቸው የጀመሩት ሽረዎች በተለይም የተጫዋች ቅያሪ ካደረጉ በኃላ የተሻለ ተጭነው ተጫውተዋል።

ካደረጓቸው ሙከራዎችም ተቀይሮ የገባው ዓወት ገ\ሚካኤል ከመስመር አሻግሮት አግዳሚውን ገጭቶ የተመለሰው ኳስ እና ፎፋና ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ አብርዶ መቶ ቋሚውን ለትሞ የተመስለሰው ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። መድሃኔ ብርሃኔ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከል ላይ አዘንብለው የተጫወቱት ሶሎዳ ዓድዎችም በአጋማሹ ሁለት የተሻለ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። ሙሉዓለም በየነ አክርሮ መቶ ወንድወሰን አሸናፊ የመለሰው እና ዓብዱሰላም የሱፍ ያደረገው ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ጨዋታው በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች በእኩል ነጥብ ምድባቸው መምራት ጀምረዋል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላም አንጋፋው ናይጀርያዊ ግብጠባቂ ሰንደይ ሮትሚ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ