ሉሲዎቹ ነገ ረፋድ ወደ ታንዛኒያ ያመራሉ

ታንዛኒያ በምታስተናግደው የሴቶች የሴካፋ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ ረፋድ ወደ ዳሬሰላም ያቀናል።

ለ4ኛ ጊዜ የሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር ዘንድሮ በታንዛኒያ ሲካሄድ ስምነት ሃገራትም ይሳተፉበታል። በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈሉት ሊሲዎቹም በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እየተመሩ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ (ሰኞ) ልምምዳቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም የጀመሩት ሊሲዎቹ ዓርብ የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከ15 ዓመት በታች የወንዶች ቡድን ጋር ማከናወናቸው ይታወሳል። ቡድኑ ዛሬ ረፋድም ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ከነገ ተስፋ ከ17 ዓመት በታች የወንዶች ቡድን ጋር አከናውኗል። ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች በማስገባት ጨዋታውን ሲያከናውን በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በተጠባባቂነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ተጨዋቾችን በማስገባት ተጫውቷል። በዚህም ሊሲዎች በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠረባቸው ሶስት ግቦች 3ለ0 ተረተዋል።

ምንም እንኳን ቡድኑ በዚህ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ቢሸነፍም የቡድኑ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በጨዋታው የቡድኑን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደለዩ እና በተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደሆኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ቡድኑ ነገ ረፋድ 3 ሰዓት ውድድሩ ወደሚደረግበት ታንዛኒያ እንደሚያመራ ታውቋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከጂቡቲ፣ ኬኒያ እና ዩጋንዳ ጋር መደልደሉ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ