ትግራይ ዋንጫ| አክሱም ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲሸጋገር መቐለ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

ዘካርያስ ፍቅሬ በዘጠነኛ ሰከንድ ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ አክሱም ከተማ ተጋጣሚውን አሸንፏል።

ዛሬ በትግራይ ዋንጫ ከተካሄዱት ጨዋታዎች ሁለተኛው የሆነው ይህ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር እና የደጋፊዎች ቀልብ የሳበ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ግብ ለማስተናገድ የፈጀበት ግዜም ዘጠኝ ሰከንድ ብቻ ነበር፤ ፈጣኑ አጥቂ ዘካርያስ ፍቅሬ ጨዋታው እንደተጀመረ ከመሃል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎች ያደረጉት አክሱሞች በአዲስዓለም ደሳለኝ እና አንተነህ ተሻገር የግብ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም በአዲስዓለም ደሳለኝ ከረጅም ርቀት የተደረገች ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በጊዜ ግብ ያስተናገዱት መቐለዎችም አቻ ለመሆን በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም እንዳለ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ ፣ ሙልጌታ ወ\ግዮርጊስ ከኦኪኪ ኦፎላቢ የተላከለት ኳስ አክርሮ መቶ በድጋሜ የራስወርቅ ተረፈ ያዳነው ኳስ እና ኄኖክ ኢሳይያስ አክርሮ መቶ የራስ ወርቅ ያዳነው እንዲሁም ያሬድ ብርሃኑ ከእንዳለ ከበደ የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰው ኳስ መቐለን አቻ ለማድረግ ያቃረበ ነበር።

የመቐለ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ምዓም አናብስት አጥቅተው የተጫወቱበት በአንፃሩ አክሱሞች አፈግፍገው ውጤት ይዘው ለመውጣት የተንቀሳቀሱበት ነበር። በአጋማሹም በበርካታ አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ሲሆን ከነዚህም ኤፍሬም አሻሞ ዮናስ ገረመው ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና አስናቀ ሞገስ አክርሮ መትቶ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም አሸናፊ ሃይሉ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረገው ሙከራ እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው በዚህ መልኩ በአክሱም 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አክሱም ከተማ ወደ ቀጣይ ዙር ሲያልፍ መቐለዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የጨዋታው ኮከብም የመቐለ 70 እንደርታው አሸናፊ ሃፍቱ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ