ደደቢት ከ አርባምንጭ ከተማ ፡ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

 

ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የደደቢት እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ነገ በ9፡00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ይደረጋል፡፡

መካከለኛ የውድድር ዘመን ጀምሮ ያደረገው ደደቢት ባለፉት 7 ሳምንታ ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ቢያስቆጥርም ተመሳሳዩን የግብ መጠን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ ሰማያዊ ጦረኞች የሊጉ ለ1 ወር መቋረጥ የተከላካይ ክፍላቸውን ላማሻሻል እድል የሰጣቸው ሲሆን የተከላካይ እና የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ከውጭ ለማስፈረም መስማማቱ ተነግሯል፡፡

ከደደቢት በኩል በጉዳት እና በቅጣት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች እንደሌለ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ሲያመለክት ጉዳት ላይ የነበሩት ዳዊት ፍቃዱ እና ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ከጉዳታቸው አገግመው የነገውን ጨዋታ ለማድረግ ብቁ ሆነዋል፡፡

በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ሲሆን ከሊጉ ወገብ በታች ለመቀመጥም ተገዷል፡፡ ቡድኑ ቁልፍ ተሰላፊዎቹን በክረምቱ ማጣቱ ምንያህል እንደጎዳውም በሜዳ ላይ ተስተውሏል፡፡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ የአንድ ወሩን የእረፍት ጊዜ ተጠቅመው በሚገባ ያልተዋሃደውን ቡድን ያሻሽሉታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአርባምንጭ ከተማ በኩል በጉዳት እና ቅጣት የነገው ጨዋታ ስለሚያመልጣቸው ተጫዋቾች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሆኗል፡፡ ሆኖም በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ደደቢትን ለቆ አርባምንጭን የተቀላቀለው ታደለ መንገሻ የቀድሞ ክለቡን ለመጀመርያ ጊዜ ይገጥማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም

ደደቢት ፡ አሸነፈ ፣ ተሸነፈ ፣ አቻ ፣ አሸነፈ ፣ ተሸነፈ

አርባምንጭ ከተማ ፡ አቻ ፣ አቻ ፣ ተሸነፈ ፣ ተሸነፈ ፣ አሸነፈ

 

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች

አርባምንጭ ከተማ ወደ ሊጉ ካደገበት 2004 የውድድር ዘመን ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 8 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ደደቢት በአርባምንጭ ላይ የውጤት የበላይነት ያለው ሲሆን ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ሰማያዊዎቹ 5 ግቦች በአርባምንጭ ከተማ መረብ ላይ አሳርፈዋል፡፡

Dedebit ArbaMinch Facts

ያጋሩ