የትግራይ ዋንጫ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ከምድብ አንድ ወላይታ ድቻ ወደ ፍፃሜው ማለፉን ያረጋገጠበትን ድል አስመዝግቧል።
የወላይታ ድቻ ብልጫ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታዩበት የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሲሆኑ ሙከራውም ከረጅም ርቀት የተደረገ ጥሩ የግብ ሙከራ ነበር። የጦና ንቦች ከመጀመርያው ሙከራ በኃላም በበርካታ አጋጠሚዎች ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም ደጉ ደበበ ከነጋሽ ታደሰ የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ የሞከረው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ቡድኑን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረበ ነበር።
በአጋማሹ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ወላይታ ድቻዎች በሃያ ሰባተኛው ደቂቃ በቸርነት ጉግሳ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግቡም ተስፋዬ አለባቸው ከረጅም ርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ከተፋው በኃላ ነበር ቸርነት ጉግሳ ደርሶ በጥሩ መንገድ ያስቆጠረው።
በአጋማሹ ብዙም የግብ ዕድል ያልፈጠሩት አክሱሞች በዮሐንስ ዓፈራ እና ዘካርያስ ፍቅሬ በኩል ሁለት ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ዘካርያስ ፍቅሬ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝንቶ ያመከነው ኳስ አክሱሞች አቻ ለማድረግ የተቃረበ ነበር።
ወላይታ ድቻዎች በትኩረት ማጣት እና በተጫዋቾች ውሳኔ አሰጣጥ ችግር በቁጥር እጅግ በርካታ የግብ ዕድሎች ያመከኑበት ሁለተኘሐው አጋማሽ አክሱም ከተማዎች የተጫዋች ለውጥ ካደረጉ በኃላ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል።
ወላይታ ድቻዎች በዚህኛው አጋማሽም ግብ ለማስቆጠር ግዜ አልወሰደባቸውም፤ በአርባ ስምንተኛው ንጋሽ ታደሰ ከረጅም ርቀት ግሩም ግብ በማስቆጠር የቡድኑ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ድቻዎች ከግቡ በኃላም በቢንያም እሸቱ እና በበረከት ወልዴ በርካታ ዕድሎች የፈጠሩ ሲሆን በተለይም ተቀይሮ የገባው ቢንያም እሸቱ ያመከናቸው የግብ ዕድሎች የግብ ልዩነቱ ማስፋት የሚችሉ ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማች በርካታ ተጫዋቾች ቀይረው ያስገቡት አክሱሞች በርካታ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። ከነዚህም ዘካርያስ ፍቅሬ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ እና ንስሃ ታፈሰ ከቅጣት ምት ያደረገው ጥሩ ሙከራ ይጠቀሳሉ።
መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠ ተጨማሪ ደቂቃም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሁለት ግቦች ተቆጥረዋል። በወላይታ ድቻዎች በኩል ቢንያም እሸቱ የተከላካይ ስህተት ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግሩም ግብ ቡድኑ ሶስት ለባዶ እንዲመራ ያስቻለች ስትሆን በአክሱሞች በኩልም አዳነ ተካ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን በባዶ ከመሸነፍ አድኖታል።
ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በውድድሩ ፎርማት መሰረት ወላይታ ድቻ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑ ሲያረጋግጥ አክሱም ከተማ ለደረጃ ይጫወታል።
በውድድሩ ጥሩ ብቃቱ እያሳየ የሚገኘው በረከት ወልዴ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ