በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተጠባቂው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 በመርታት በመጪው እሁድ ከሰበታ ከተማ ጋር ለፍፃሜ ተፋላሚ መሆን ችሏል።
የኢትዮጵያ ቡናዎች በጫና ውስጥ ኳስን መስርቶ የመውጣት አቅም በእጅጉ በተፈተነበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ስህተት በተገኙ ሁለት ግቦች ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል።
ጨዋታውን በክብር እንግድነት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአዲስአበባ ከተማ እግርኳስ ፌደሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን አስጀምረውታል።
በዛሬው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከዚህ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች ከገጠሟቸው ክለቦች በተለየ ለየት ባለ አቀራረብ በቀረበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በእጅጉ ሰፈተኑ አምሽተዋል። በቀደሙት ጨዋታዎች ቡናን ከገጠሙት ተጋጣሚዎች በተለየ ጊዮርጊሶች ኢትዮጵያ ቡና ኳስን ከግብ ጠባቂያቸው መስርተው እንዳይወጡ ከፍተኛ ጫና በማሳደር የቡና ተጫዋቾች ስህተት እንዲሰሩ ያስገደዱበት መንገድ የተዋጣላቸው ነበሩ።
ጨዋታው እንደተጀመረ ጋዲሳ መብራቴ ባደረገው አስደንጋጭ ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች ጊዮርጊሶች የተሻሉ የነበሩት ነበር ሆኖኝ በ12ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ባጋጠመው ጉዳት በአቤል ያለው ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።
እንደከዚህ ቀደም ጨዋታዎች በርካታ የኳስ ቅብብሎችን ለማድረግ የተቸገሩት ቡናዎች 25ኛው ደቂቃ አላዛር ከመስመር አሻምቶት የጊዩርጊሱ ግብጠባቂ የተሳሳተውንና ሚኪያስ መኮንን ሳይደርስበት ከቀረው ሙከራ ውጭ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው ተስተውለዋል።
በመጀመሪያ አጋማሽ ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በጋራ በቅብብል ሲያዜሙ የተስተዋሉበት አጋጣሚ ትኩር ሳቢ ክስተት ሆኖ አልፏል።
በ43ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ለማስጀመር ጥረት ሲያደርጉ የቡናው ሚኪያስ መኮንን በጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጫና ውስጥ በመግባቱ የተነሳ የተሳሳተውን ተጠቅመው ሁለቱ የቀድሞ የደደቢት ተጫዋቾች የአብስራና አቤል በግሩም ቅብብል አንድ ሁለት ያለፉትን ኳስ አቤል ያለው በግሩም አጨራረስ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከእረፍት መልስ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በተመሳሳይ በ55ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ የግቡን ለቆ ከፈቱዲን ጀማል ጋር ለመቀባበል ጥረት ሲያደርግ የተነጠቀውን ኳስ የአብስራ ተስፋዬ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኃላም ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በኤንዶ አቱሳይ፣ ሳልሀዲን ሰኢድ አቡበከርና አቤል ያለው አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን አምክነዋል።
በዛሬው ጨዋታ ላይ የፈረሰኞቹ አዲስ ፈራሚዎች ሀይደር ሸረፋና ደስታ ደሙ ተቀይረው በመግባት የመጀመሪያ የሲቲ ካፕ ጨዋታቸውን ለአዲሱ ክለባቸው አድርገዋል። ምንም እንኳን ሀይደረ ሸረፋ ተቀይሮ በገባ በ9 ደቂቃ ልዩነት ከቡና ተጫዋች ጋር ለፀብ በመጋበዙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ለመሰናበት ቢገደድም።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በአብዛኛው በሀገራችን ቡድኖች ሲደረግ በማይስተዋል መልኩ በጫና ውስጥ ስህተቶች ቢሰሩም ደቂቃዎች እየገፉ ቢሄድም ይዘውት ለገቡት የጨዋታ እቅድ 90 ደቂቃ ሙሉ ታማኝ ሆነው ጨርሰዋል።
ጨዋታው በፈረሰኞቹ 2-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው እሁድ ሰበታ ከተማ የሚገጥም ይሆናል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አቤል ያለው የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ