ዛሬ በትግራይ ዋንጫ በብቸኝነት የተደረገው የሶሎዳ ዓድዋ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ጥሩ ፉክክር እና በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች በታዩበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ታይቷል። በመጀመርያው አጋማሽ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩትም ሲዳማ ቡናዎች ነበሩ ፤ ሙከራውም ግርማ በቀለ ከቆመ ኳስ ያደረገው ነበር። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ሲዳማዎች በዮናታን ፍስሃ እና በሃብታሙ ገዛኸኝ ጥሩ የማግባት ዕድሎች ፈጥረው ነበር በተለይም ሃብታሙ ገዛኸኝ በተከላካዮች ስህተት ያገኘው ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ በመገናኘት መቶ ሰንደይ ሮትሚ በጥሩ ብቃት ያዳነው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር።
ሶሎዳ ዓድዋዎችም በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ሃይሉሽ ፀጋይ መቶ ግብጠባቂው የመለሰው ፣ ዓብዱሰላም የሱፍ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶ መሳይ አያኖ በጥሩ ብቃት ያወጣው እና ኤርምያስ ብርሃነ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥሩ ፉክክር የታየበት ይህ አጋማሽ በቁጥር የተሻለ ሙከራዎች እና የሲዳማ ቡናዎች ብልጫ ያስመለከተን ነበር። በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩትም ሶሎዳ ዓድዋዎች ነበሩ ፤ ሙከራውም በጋናዊው እድሪስ ዓብዱልናፊ አማካኝነት የተደረገ ነበር። ከዚህ ውጭ ሃይልሽ ፀጋይ ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራ እና ተቀይሮ የገባው አላዛር ዘውዱ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ ተጫዋች አታሎ መቶ መሳይ አያኖ በጥሩ ብቃት ያዳናት ኳስ ይጠቀሳሉ።
ብልጫ የነበራቸው እና በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት ሲዳማ ቡናዎችም በቁጥር በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አዲስ ተስፋየ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝንቶ ያመከነው ኳስ ፣ ሃብታሙ ገዛኸኝ ከመአዝን የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ መብራህቱ ሃ\ስላሴ ከመስመር ያዳነው ኳስ እና ዳዊት ተፈራ ከቅጣት ምት ያደረገው ኳስ ይጠቀሳሉ።
ከዚ ውጭም በጨዋታው መገባደጃ ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ ከሃብታሙ ገዛኸኝ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሰንደይ ሮትሚ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው ኳስም ሲዳማ ቡና መሪ ለማድረግ የተቃረበ ኳስ ነበር።
ጨዋታው በዚ መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ የተለያዩት ሶሎዳ ዓድዋዎች ምድባቸው መምራት ጀምረዋል። በጨዋታውም የሲዳማ ቡናው አማካይ ዮሴፍ ዮሃንስ ኮከብ ሆኖ ተሸልሟል።
© ሶከር ኢትዮጵያ