በምድብ ሁለት ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወልዋሎን 1ለ0 በመርታት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በሰበታ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ውስጥ ሰይፈ ዛኪርን አስወጥተው በሚኪያስ መኮንን ብቻ ሲተኩ በአንፃሩ ወልዋሎዎች ደግሞ ካርሎስ ዳምጠው፣ ሳሙኤል ዮሐንስና ሰመረ ሃፍታይን በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።
እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ ኢትዮጵያ ቡና ልክ እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ በርካታ የኳስ ቅብብሎችን በተለይ በራሱ የሜዳ አጋማሽና በመሀል ሜዳ አካባቢ ቢያደርጉም ኳስ ሲያጡ የሚሰበሰቡትን የወልዋሎ ተጫዋቾችን በመሀልም ሆነ በመስመር ለማስከፈት ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽጨበኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል የተደረገችው ብቸኛ ሙከራ እንዳለ ደባልቄ ከሳጥን ውጭ በቀጥትታ አክርሮ የመታትና ኢላማዋን ሳትጠብቅ የቀረችው ኳስ ነበረች።
ወልዋሎዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ከራሳቸው ሜዳ እንዳይጀምሩ ለማድረግ እንዲሁም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ቡናዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ያቀዱ ቢመስልም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤታማ አልነበሩም።
በ32ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎዎች በራምኬል ሎክ አማካኝነት ከቀኝ መስመር ያሻገረውን የቅጣት ምት ሳሙኤል ዩሀንስ በጭንቅላት በመግጨት የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ የለተመችው ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ የተመለከትነው ጠንካራ ሙከራ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት አድርገዋል። ወልዋሎዎች እጅግ ፈጣን የሆነውን አጥቂያቸው ጁሊያስ ናንጂቡ ፍጥነት ላይ ለመጠቀም በማሰብ ወደ መሀል ሜዳ ከተጠጋው የቡና ተከላካዮች ጀርባ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል የቡናን የመከላከል አደረጃጀት ሲፈትሹ አምሽተዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በአላማ ኳሶችን ወደ ፊት በመቀባበል የግብ እድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ጨዋታውን ማሸነፍ የግድ የሚላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከሳጥን ውጭ አከርሮ መቶ ኬይታ ያዳነበት እንዲሁም ከደቂቃዎች በኃላ ፍቅረየሱስና እንዳለ በማራኪ አንድ ሁለት ቅብብል ከገቡ በኃላ እንዳለ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ተጠቃሽ ናቸው።
በስተመጨረሻም ቡናዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በግሩም ቅብብል የተገኘውን አጋጣሚ አቤል ከበደ ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናዎች 1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ተስፋቸው ዳግም ለምልሟል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ