ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ ላልተወሰነ ጊዜ የስታዲየም ለውጥ አደረጉ

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ መሠረት ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ ሜዳቸው በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ለተወሰነ ጊዜ የሜዳ ለውጥ እንደሚያደርጉ ተረጋግጧል።

የሁለቱም ክለቦች ስታዲየምን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች እየተከወኑ ቢገኙም ግንባታቸው በሚጠበቀው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ለተወሰኑ ወራት በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በተቀያሪ ሜዳ የሚያደርጉ ይሆናል።

ስሑል ሽረዎች በቅርቡ የስታዲየማቸውን የመጫወቻ ሜዳ ሳር ለማልበስ የቁፋሮ ስራዎችን ቢያስጀምሩም ሳር ለማልበስ ከሚፈጀው ጊዜ አንፃር ሜዳው ለሊጉ ጅማሮ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። በዚህም በአማራጭነት ባስመዘገቡት የመቐለው ትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል። ሦስት የሜዳቸውን ጨዋታዎች ከ150 ርቀት በሚገኝ ሜዳ እንዲጫወቱ ቅጣት ያለባቸው ሽረዎች ቅጣቱን ሲጠናቀቁ ሜዳቸው እንደሚደርስ በባለሙያ ቢገለፅም ባለው ነባራዊ ሁኔታ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ የሚቆዩ ይሆናል ተብሏል።

ለዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በተሟላ ሁኔታ ሳይሰራ የተጓተተው የዓዲግራት ስታዲየም የግንባታ ሂደት መሻሻሎችን ቢያሳይም አሁንም በተጠበቀው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ወልዋሎም እንደ ስሑል ሽረ ሁሉ በትግራይ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል።

የመያዝ አቅሙን ለማሳደግ በርካታ የማስፋፊያ ስራዎች እየተከወኑለት የሚገኘው የወልዋሎ ስታደዮም የሣር ተከላው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ቢሆንም የመሮጫ ትራክ እንዲሁም የተመልካች መቀመጫ ወንበሮች ተከላን የመሳሰሉ ቀሪ ስራዎች እንዳሉበት ተገልጿል። በተጨማሪም ሜዳው ሣር አሁን ካለበት የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስና ጥቅጥቅ ብሎ እንዲበቅል ለማስቻል ሁለት ዙር አጨዳ እንደሚቀረው ተገልጿል። ስራው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ