ሁለት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በተለዋጭ ሜዳ እንዲያከናውኑ ተወሰነ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐቢይ ኮሚቴ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችን ሜዳ ሲገመግም ቆይቶ የተወሰኑ ክለብ ሜዳዎች ብቁ ባለመሆናቸው ላልተወሰነ ጊዜ በተለዋጭ ሜዳ እንዲጫወቱ ከውሳኔ ደርሷል።

በግምገማው ውጤት መሠረት በዘንድሮ ውድድር አመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ሰበታ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ የሜዳቸውን ደረጃ እስኪያሻሽሉ ድረስ በሜዳቸው እንዳይጫወቱ ውሳኔ ተላለፈባቸው ክለቦች ሆነዋል። ከመጫወቻ ሜዳ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው በግምገማው የተገለፀው የሰበታ ስታዲየምና የወልቂጤ ስታዲየምም መስፈርቱን እስኪያሟሉ ድረስ በምትክነት ክለቦቹ በአማራጭነት ባስያዟቸው ሜዳዎች የሚጫወቱ ይሆናል።

ሰበታ ከተማ በዕድሳት ላይ የሚገኘው የሰበታ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ አዲስ አበባ ስታዲየም ወይም ሌላው በአዲስ አበባ የሚገኘው አበበ ቢቂላ ስታዲየምን በአማራጭነት ያቀረበ ሲሆን ሌላኛው አዲስ አዳጊ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በርካታ አማራጮችን እያጤነ ሲሆን የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን ግን በሆሳዕናው አቢዮ አርሳሞ ስታዲየም ሊያከናውን እንደሆነ ታውቋል።

ሰበታ ከተማ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን በአንደኛው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ሲያደርግ ወልቂጤ ከተማም በተመሳሳይ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን በአንደኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያከናውን ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ