“የብሔር ስያሜን ይዘው የተቋቋሙ ክለቦችን አንመዘግብም” አቶ ኢሳይያስ ጂራ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ትላንት በአዳማ በተደረገው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉባዔ ላይ በዘር እና ብሔር ስያሜ የተቋቋሙ ክለቦችን አንመዘግብም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የክለብ ፕሬዝዳንቶች፣ የስፖርቱ መሪዎች፣ የደጋፊ ተወካዮች፣ ዳኞችና ኮሚሽነሮች እና ሌሎች በርካታ ባለድርሻ አካላትን አሳታፊ ባደረገውና በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት በተሰናዳው የስፖርታዊ ጨዋነት የውይይት መድረክ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለእግርኳሱ ዕድገት ማነቆ ከሆነው የፖለቲካ ሽኩቻ በተጨማሪ በዘር እና ብሔር ስያሜ የተደራጁ ክለቦች ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ ገልፀዋል። “ሁላችንም ለእግርኳሱ ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ በመቆርቆር ለሰላማዊ ተግባር ብቻ ልናውል ይገባል። ሁላችንም ከተረባረብን የማይለወጥ የለም። በኛ በኩል ብሔርን ማዕከል በማድረግ እና በዘር ስያሜ የተቋቋሙ መጠሪያ ስያሜዎችን የያዙ ክለቦችን አንመዘግብም። ተለዋጭ መጠሪያ ስያሜን እስከ ቅርብ ቀን አሳውቁን” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ