አአ ከተማ ዋንጫ | መከላከያ በወልቂጤ ሽንፈት ቢያስተናግድም ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተሸጋግሯል

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ አንደኛ ሳምንቱን ሲያስቆጥር ከምድብ ሀ ሦስተኛ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የመከላከያ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በወልቂጤ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መከላከያ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከተጠቀመባቸው ተሰላፊዎችን ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ ብዙም እድል ባላገኙ ተጫዋቾች ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ ከምድቡ መሰኔበቱን ያረጋገጠው ወልቂጤ ከተማ መጠነኛ ለውጦች አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቷል።

የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ወልቂጤ ከተማ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበረው ሲሆን በበርካታ ጎል ሙከራዎች ባይታጀብም በተደጋጋሚ ወደ መከላከያ ግብ በመድረስ ያልተሳኩ የማጥቃት ሙከራዎችን አድርገዋል። በ11ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ከአጥቂ ክፍል ተጣማሪው ጃኮ አራፋት የተመቻቸለትን ጥሩ እድል ከጠባብ አንግል መትቶ ወደ ጎል ያመራችውን ኳስ ሙሉቀን ከጎሉ መስመር ያወጣት ወልቂጤን መሪ ልታደርግ በእጅጉ የተቃረበች ነበረች።

ወልቂጤዎች የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት በ18ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል። ከርቀት ወደ ጎል የተላከውን ኳስ የመከላከያ ተከላካዮች በአግባቡ ባለማራቃቸው አልመድ ሁሴን አግኝቶ ሲመታው በተከላካዮች በድጋሚ ተደርባ የደረሰችውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጃኮ አራፋት በመልካም አጨራረስ ባስቆጠራት ጎል ነበር መሪ መሆን የቻሉት።

ከጎሉ በኋላ መከላከያዎች ቀጣዮቹን ጥቂት ደቂቃዎች የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም በ26ኛው አቤል ነጋሽ ከግማሽ ጨረቃ አካባቢ አክርሮ ወደ ጎል መትቶ አግዳሚው ከገጨበት ሙከራ በኋላ ግን መልሰው ተቀዜቅዘዋል። በአንፃሩ ወልቂጤዎች በጎል ሙከራዎች ባይታጀብም በኳስ ቁጥጥር እና ወደ ጎል በመድረስ የተሻለ ተንቀሳቅሰው የመጀመርያው አጋማሸን በመሪነት አጠናቀዋል።

በሁለኛው አጋማሽ መከላከያዎች ፍሬው ሰለሞን፣ በኃይሉ ግርማ እና ሀብታሙ ወልዴን ጨምሮ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎችም ተጭነው መጫወት ችለው ነበር። በተለይ በ46ኛው ደቂቃ ፍሬዝ ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ቅርብ ርቀት ግልፅ ማግባት ዕድል አግኝቶ ለጥቂት ቋሚውን ታኮ የወጣበት አስቆጪ ሙከራ ነበር። በሒደት ጨዋታውን መልሰው የተቆጣጠሩት ወልቂጤዎች በ57ኛው ደቂቃ ጥሩ የማግባት እድል በጃኮ አራፋት አማካኝነት ፈጥረው ቶጓዊው አጥቂ የግቡ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።

ጨዋታው አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ በ83ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት ከሙሀጅር መኪ የተቀበለውን ኳስ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት በግሩም አጨራረስ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ጨዋታውም በወልቂጤ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ሽንፈት ቢያስተናግድም በቀጣዩ ጨዋታ በተመሳሳይ ሽንፈት ካስናገደው ባህር ዳር ከተማ ጋር በእኩል ነጥብ እና ጎል ልዩነት ላይ በመገኘቱ በዕጣ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል። የጨዋታውን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ጃኮ አራፋትም የጠዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ