አአ ከተማ ዋንጫ| ፈረሰኞቹ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል

የምድብ 1 ሶስተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ 10:30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህር ዳር ከተማን 3ለ1 በማሸነፍ የምድቡ የበላይ በመሆን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር ከተማን በማሰልጠን ላይ ለሚገኘው የቀድሞው የክለቡ ተጫዋች አና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባበረከቱት የማስታወሻ ስጦታ በተጀመረው ጨዋታ ሶስት ሶስት የፊት መስመር አጥቂዎችን ወደ ሜዳ ይዘው የገቡት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ግልፅ የግብ ማግባት እድል ለመፍጠር ተቸግረው ታይቷል። ምንም እንኳን ሁለቱም ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎችን መሰንዘር ባይችሉም አልፎ አልፎ በግዙፎቹ አጥቂዎቻቸው ሳላዲን ሰዒድ እና ማማዱ ሲዲቤ አማካኝነት ሙከራዎችን በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች አድርገዋል።

ጨዋታው ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ያስተናገደው በ35ኛው ደቂቃ ነው። በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው አቡበከር ሳኒ ከመሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ከደቂቃዎች በኋላም ለተሰነዘረባቸው አስደንጋጭ ሙከራ ምላሽ ለመስጠት ወደ ፈረሰኞቹ የግብ ክልል ያመሩት የጣና ሞገዶቹ በፍፁም ዓለሙ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል።

በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገታ አድርገው በተረጋጋ ሁኔታ ቅብብሎሽ ለመፈፀም ጥረት አድርገዋል። በተቃራኒው ባህር ዳር ከተማዎች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ለማግኘት ከራሳቸው ሜዳ በመውጣት ተጭነው ኳስ ለመቀማት ጥረት አድርገዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ከፍቅረሚካኤል አለሙ የተላከለትን የቅጣት ምት ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ 0-0 ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታው ግብ ለማግኘት በተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በርከት ያሉ የግብ እድሎችም በአጋማሹ ተፈጥረው ታይቷል። በአንፃራዊነት ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች እጅግ ተጠናክረው በመግባት በአጋማሹ ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

በ53ኛው ደቂቃ ሳላምላክ የተሳሳተውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጋዲሳ መብራቴ የሞከረው እንዲሁም በ56ኛው ደቂቃ የባህር ዳር ተጨዋቾች የፈጠሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ዛቦ ቴጉይ የሞከረው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተፈጠሩ የግብ እድሎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ሙከራዎች የተደናገጡ የሚመስሉት የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጨዋቾች በትኩረት ማነስ ተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶችን ሲፈፅሙ ታይቷል።

በ60ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ያመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያሻሙትነን ኳስ ጌታነህ ከበደ አግኝቶት ሲሞክረው የባህር ዳር ከተማ የመስመር ተከላካይ ሚኪያስ ግርማ በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጌታነህ ከበደ መቶት ግብ ጠባቂው ሃሪስተን ሄሱ አድኖበታል፣ ነገር ግን ጌታነህ ኳሱን ከመምታቱ በፊት ሁለት የባህር ዳር ከተማ ተጨዋቾች ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ በመግባታቸው የፍፁም ቅጣት ምቱ እንዲደገም ተደርጓል። በዚህም ጌታነህ ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘውን እድል ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን በ62ኛው ደቂቃ መሪ አድርጓል።

ከፍፁም ቅጣት ምቱ በኋላ እጅግ ጨዋታውን መቆጣጠር የከበዳቸው ባህር ዳሮች ከአምስት ደቂቃ በኋላ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በዚህ ደቂቃ ሳላዲን ሰዒድ ከሙላለም መስፍን የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የጊዮርጊሶችን የበላይነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ከሶስት ደቂቃ በኋላ መሃል ሜዳ ላይ የቅጣት ምት ያገኙት ባህር ዳር ከተማዎች አጋጣሚውን የግብ ማስቆጠሪያ ምንጭ አድርገው የመሪነቱን ልዩነት አጥበዋል። በ70ኛው ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት አምበሉ ፍቅረሚካኤል አለሙ ለዜናው ፈረደ አሻግሮለት ዜናው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል። ባህር ዳሮች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀን በሚሞክሩበት ጊዜ አብዱልከሪም መሃመድ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን መልሶ አስፍቶባቸዋል።

ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት የቅጣት ምት ያገኙት ባህር ዳሮች አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለመቀየር በዳንኤል ኃይሉ አማካኝነት ኳሱን አሻምተውት ወደ ግብ የቀረቡ ቢመስልም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች በቀሩት ሰዓት የባህር ዳር ከተማ ምክትል አሰልጣኝ ታደሰ ጥላሁን የዳኛ ውሳኔ ተቃውመህ አላስፈላጊ ተግባር አሳይተሃል በሚል በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ጨዋታውን ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀጣይ ዙር በአንደኝነት ሲያልፍ ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ከመከላከያ ጋር በነጥብ እና በጎል እኩል በመሆኑ በተከናወነ የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ተሸንፎ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቡበከር ሳኒም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ