ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ሲጠናቀቅ 7:00 ላይ በተደረገው የደረጃ ጨዋታ አዳማ ከተማ በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች ፋሲልን አሸንፎ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡
ሁለቱም ቡድኖች በምድብ እና ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን በርካታ ተጫዋቾች ለውጠው የገቡ ሲሆን በመጀመርያው የጨዋታ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት ነበር። በተለይ አጥቂው ሚካኤል ጆርጅ እና ኃይሌ እሸቱ በመስመር በኩል በሚያደርጉት መልካም እንቅስቃሴን ማድረግ ቢችልም ንፁህ የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ግን መመልከት አልቻልንም።
ሚካኤል ጆርጅ በቀኝ በኩል ሰጥቶት ኃይሌ እሸቱ ከግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጋር ተገናኝቶ ብረት የመለሰበት እና ከቅጣት ምት ሚካኤል ጆርጅ ያገኛት እና ወደ ግብ መትቶ የተመለሰበት ተጠቃሽ ሁለት ሙከራዎች ሲሆኑ በአንፃሩ ዐፄዎቹ ከማጥቃት ይልቅ አጋማሹን በኳስ ንክኪ ብቻ የተገደበ አጨዋወትን ተከትለዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የኳስ መንሸራሸሮችን በሜዳ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ቢያሳዩንም ኢዙ አዙካ በፋሲል በኩል ከቅጣት ምት መቶ ለጥቂት የወጣችበት እና ሚካኤል ጆርጅ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ተስፋዬ ነጋሽ ሰጥቶት ተስፋዬ ያመከናት ኳስ በጉልህ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሁለት የአጋማሹ ሙከራዎች ናቸው።
ፋሲል ከነማዎች በተለይ ሙጂብ ቃሲምን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ተጨማሪ ዕድሎቸን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም መደበኛው ክፍለ ጊዜ ያለግብ 0-0 በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት የፋሲሎቹ አምሳሉ ጥላሁን እና እንየው ካሳሁን የመለያ ሲያመክኑ በአዳማ በኩል ቴዎድሮስ በቀለ ብቻ በመሳቱ አዳማ ከተማ 4-2 አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሀስ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ