ለአንድ ሳምንት ያህል በአዳማ ከተማ አስተናጋጅነት ሲደረግ በቆየው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ሀዋሳ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 በመርታት በውድድሩ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
9:30 ሲል የተጀመረው ጨዋታ ማራኪ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕናዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ አጥቂዎቹ በመጣል እና ጫናን በማሳደር፣ ሀዋሳዎች ደግሞ በሁለቱም መስመሮች በኩል ሰብሮ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት የተሻሉ መሆናቸው ተስተውሏል።
ሀዋሳዎች በተደጋጋሚ በመስመር በኩል በብርሀኑ በቀለ አማካኝነት የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ሰምሮ 23ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ከቅጣት ምት አማካዩ ዘላለም ኢሳይያስ በረጅሙ ሲያሻማ አዲስዓለም ተስፋዬ በግንባር ገጭቶ ያመቻቸውን ብርሀኑ ወደ ግብነት ለውጧት ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡
ከግቧ በኃላ ሀዋሳዎች በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ብሩክ በየነን ማዕከል በማድረግ ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ይህ የጨዋታ መንገዳቸውም በሀዲያ ሆሳዕናዎች ብልጫ እንዲወሰድባቸው አድርጓል፡፡ ሆሳዕናዎች በተለይ በሙሳ ካመራ ቢስማርክ አፒያ አማካኝነት ከአማካዩ አፈወርቅ እና ሄኖክ አርፊጮ በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ሲያጠቁ ያስተዋልን ሲሆን አፈወርቅ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ ቢሊንጌ በግሩም መልኩ ያወጣበት ኳስ ሆሳዕናን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች፡፡
ከእረፍት መልስ ሀድያ ሆሳዕና አቻ ለመሆን ፍፁም ብልጫን ወስዶ መጫወት ቢችልም የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ለማስቆጠር ግን አልቻለም፡፡ ግብ ለማስቆጠር ያለመ በሚመስል መልኩ ተከላካዩን በረከትን አስወጥተው አጥቂው ቢስማርክ ኦፖንግን በማስገባት የአጥቂ አማራጫቸውን ያሰፉት ሆሳዕናዎች ጠጣሩን የሀዋሳ ተከላካይ አልፈው አቻ መሆን ግን አልቻሉም።
በኃይሉ ተሻገር 86ኛው ደቂቃ ላይ ያገኛትን ግልፅ አጋጣሚ በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ተወርውሮ ያወጣት ኳስ በስተመጨረሻ ከታዩት መካከል አስቆጪ ዕድል ነበረች፡፡ በጭማሪው ሰዓት ተቀይሮ የገባው ቸርነት አውሽ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችን ኳስ ከግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሀዋሳን የግብ መጠን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም በቀላሉ አምክኗታል፤ ጨዋታውም በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በውጤቱ መሠረት ከስምንት ዓመት በፊት በ2005 ውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ ሲደረግ አዳማ ከተማን በማሸነፍ ዋንጫ ያነሳው ሀዋሳ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ውድድሩን በቻምፒዮነት ፈፅሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአዳማ ከተማ ስፖርት ኮሚሽነር ተስፋዬ እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የሽልማት ስነስርዓት ተከናውነዋል፡፡ ለተሳታፊዎች እና አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም የምስክር ወረቀት ስጦታ ተበርክቷል፡፡
1ኛ፡ ሀዋሳ ከተማ – የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እና የዋንጫ ባለቤት
2ኛ፡ ሀዲያ ሆሳዕና – የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ እና የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ
3ኛ፡ አዳማ ከተማ – የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ
ኮከብ ተጫዋች – አለልኝ አዘነ (ሀዋሳ ከተማ)
ከፍተኛ ግብ አግቢ – ሙጂብ ቃሲም እና ኦሴይ ማውሊ (3 ጎሎች ከፋሲል ከነማ)
ኮከብ አሰልጣኝ – አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)
የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ – ሀዲያ ሆሳዕና
© ሶከር ኢትዮጵያ