የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-1 ሀዋሳ ከተማ

3ኛው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ሀዋሳ ከተማ ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ቻምፒዮን ሆኗል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ስለጨዋታው እና በውድድሩ ላይ ስለነበራቸው ቆይታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” በጨዋታዎቹ ላይ ለማየት የምፈልገውን ነገር አይቻለው” አዲሴ ካሴ

ስለጨዋታው እንቅስቃሴ

ተጫዋቾቼ በየጨዋታው የነበራቸው የማሸነፍ ፍላጎት ስኬታማ አድርጎናል። ተጋጣሚያችን ሀዲያ ሆሳዕና እጅጉን ጠንካራ ቡድን ነው። ሆኖም ተጫዋቾቼ የሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተዋል። በተጨማሪም ሆሳዕና ከፋሲል ሲጫወት በደንብ አይተነው ነበር። ቡድናችንን በዛ መልክ ነው ያዘጋጀነው። የተጫዋቾቼ የማሸነፍ ፍላጎትም ስኬታማ አድርጎናል።

ስለ ውድድሩ ቆይታቸው

የአዳማ ውድድር ለኛ በጣም ነው የረዳን። ቡድናችን ልምምዱን ሲያደርግ የነበረው በሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ነበር። በተፈጥሮ ሳር ላይ ቡድኑ ምን ይመስላል የሚለውን እየተመለከትን፤ ከጨዋታ ጨዋዎፀታ እያሻሻልን እዚህ ደርሰናል። አሁን ይበልጥ ባየነባቸው ክፍተቶች ሰርተን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ብቅ እንላለን።

” ውድድሩ ከወዲሁ ድክመት እና ጥንካሬያችንን እንድናውቅ ረድቶናል” ግርማ ታደሰ
ስለጨዋታው እንቅስቃሴ

ዛሬ ካደረግናቸው ጨዋታዎች ሁሉ እጅጉን የተሻለ ነበር። በአዳማው ውድድር ቡድኑ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ነው የመጣው። ዛሬ እስካሁን ካደረግናቸው ጨዋታዎች ሁሉ እጅጉን የተሻልን ነበርን። ተጋጣሚያችን በቀላሉ ጎል እንዳይቆጥርበት በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር እጅግ በዝተው መጫወት መቻላቸው ያገኙትን የግብ እድል ደግሞ የኛም ስህተት ታክሎበት አስቆጠሩ እንጂ በእንቅስቃሴም ሆነ በርካታ የግብ ዕድል በመፍጠር የተሻለ ነበርን።

ስለ ቆይታቸው

በአዳማ ቆይታዬ ፕሪምየር ሊጉ ምን ይመስላል የሚለውን አይቼበታለው። በሙሉ ተሳታፊ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ብዙ ቆይታ ያላቸው ናቸው። ከዛ አንፃር ፕሪምየር ሊጉ ውስጥ ተፎካካሪ መሆን የሚችል ቡድን ነው። የሲቲ ካፑ መኖር ክፍተታችንን እንዲሁም ጥንካሬያችንን ለይቸበታለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ