አአ ከተማ ዋንጫ | ኢትዮጵያ ቡና በግማሽ ፍፃሜው ጊዮርጊስን ይገጥማል

ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለግብ አቻ ቢለያይም ሰበታ ከተማን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መሸጋገር ችሏል።

በዛሬው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከብሔራዊ ቡድን መልስ ተክለማርያም ሻንቆ እና አማኑኤል ዮሐንስን በመጀመሪያ 11 ውስጥ በማካተት ጨዋታውን ሲጀምሩ በአንፃሩ በኤሌክትሪኮች በኩል ባሳለፍነው ጨዋታ የተጠቁሙበትን ተመሳሳይ ቡድን በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድንና በጉዳት ያጡት ቡናዎች ገና በማለዳ የመሀል ተከላካያቸው ወንድሜነህ ደረጀን ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ በኢብራሂም ባጃ ለመቀየር ተገደዋል።

እንደመጀመሪያ ጨዋታዎች ሁሉ ዛሬም ኢትዩጵያ ቡናዎች ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል ለመጀመር በሚያደርጉት ጥረት በተከላካይ አማካዩና በመስመር ተከላካዮቹ ደካማ የቦታ አያያዝ ኳስን በሚፈለገው መልኩ ለማስጀመር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

በ6ኛው ደቂቃ እሸቱ መናን የተነጠቀውን ኳስ ያብቃል አመቻችቶ ለእንዳለ አቀብሎት እንዳለ የመታውና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ የኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ያደረጉት ብቸኛ ጠንካራ ሙከራ ነበር።

በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች በአመዛኙ የመጀመሪያ አጋማሽ ከኳስ ውጭ ጠቅጠቅ ብለው በ4-5-1 ቅርፅ ለመከላከልና በተገኘ አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ26ኛው ደቂቃ በግሩም የመልሶ ማጥቃት አዳም አባስ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ በረከት ይስሀቅ ሳይጠቀምበት የቀረችው አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በቡና ተጫዋቾች በኩል በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የተደረጉት ቅብብሎች በአመዛኙ ከኤሌክትሪኮች ሁለቱ በቅርብ ርቀት ከቆሙት የመከላከል መስመሮች ፊት የተደረጉ በመሆናቸው ኳሶቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ አርጓቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው የተለየ መልክ ነበረው፤ በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ከቡና በተሻለ ከፍ ባለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ተቆጣጥረው መጫወት ችለዋል። በዚህም በ50ኛው ደቂቃ ተስፋዬ ሽብሩ ከማእዘን የተሻማው ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ሳይጠቀም የቀረበት እንዲሁም በ75ኛው በተመሳሳይ ሐብታሙ መንገሻ በጭንቅላቱ ያመከኗቸው ኳሶች ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ኤሌክትሪኮች የተሻሉ በነበሩበት በዚሁ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ78ኛው ደቂቃ አላዛር ሽመልስ ከቀኝ አጥብቦ በመግባት የሞከረውና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ ውጭ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲቸገር ተስተውሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል ጉዳት አስተናግዶ ወጥቷል። በዚህም በዛሬው ጨዋታ ሁለት የመጀመሪያ ተመራጭ የመሀል ተከላካዮቹን በጉዳት ማጣቱ እጅግ አስደንጋጭ ዜና ሆኗል።

ጨዋታው 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በአራት ነጥብ ከምድብ ሁለተኛ በመሆን ሰበታን ተከትሎ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል፤ ፈቱዲን ጀማልም ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ የዕለቱ ኮከብ በመባል ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ