ዐምና ጥሩ ቡድን በመገንባት እስከመጨረሻ ሳምንታት ተፎካካሪ የነበረው ኢትዮጵያ መድን በርካታ ተጫዋቾቹን በፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊጉ መነጠቁን ተከትሎ ቡድኑን በአዲስ መልክ ለመገንባት ተገዷል።
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ የፎርማት ለውጥ አድርጎ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ለውጡ ውድቅ በመደረጉ በዝውውር ጉዳይ እክል ቢገጥመውም አሁን ላይ ችግሩን ፈትቶ 21 ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን በአዲስ መልክ ማዋቀሩን አስታውቋል።
ጅማ አባጅፋር በ2009፣ ሰበታ ከተማ 2011 ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ የቡድኖቹ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የነበረው ቢንያም ታከለ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክን ጨምሮ ለበርካታ ክለቦች የተጫወተው ሙሴ ገብረኪዳን ከደሴ ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ልደታ ክፍል ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ሄኖክ መብራቱ ሄኖክ ቡድኑን የተቀላቀሉ ግብ ጠባቂዎች ናቸው።
ይደነቁ የሺጥላ ከቡራዩ፣ ከቀድሞ አሰልጣኙ መልሶ የመስራት እድል ያገኘው አስናቀ ተስፋዬ ከለገጣፎ፣ ኢብራሂም ሁሴን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን እና ደደቢት ተጫዋች ብርሃኑ ቦጋለ ከወልዋሎ፣ ሚፍታህ ዐወል ከቤንች ማጂ ቡና እና አላምዱህ ሀሰን ከ ከመድን ተስፋ ቡድን ክለቡ በተከላካይ ስፍራ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ናቸው።
በኢኮስኮ ጥሩ ቆይታ የነበረው ዳንኤል ታደሰ፣ ኩማ ደምሴ ከደደቢት፣ አብዱልቃድር ከድር ከቡራዩ፣ ጅላሎ ሻፊ ከስሑል ሽረ፣ ሄኖክ አንጃ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ኢትዮጽያ መድን ያመሩ የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ናቸው።
በአጥቂ ስፍራ ላይ ጅማ አባጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ አባል የነበረው አቅሌሲያስ ግርማ በመከላከያ፣ በቡታጅራ እና ሀላባ ቆይታ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ኤፍሬም ቶማስ፣ አብዱልናስር ፈቱዲን ከወልቂጤ፣ ቶሎሳ ንጉሴ ከቡራዩ፣ ኤፍሬም ቀሬ ከአክሱም እንዲሁም ከመድን ተስፋ ቡድን ካሳሁን ሰቦቃ በመድን የምናየቸው ይሆናል።
በተያያዘ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ የሚመራው ክለቡ ከአምናው ስብስቡ የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሷል። ሂደር ሙስጣፋ፤ ዮናስ ብርሃኑ፣ ጌትነት ተስፋዬ እና በኃይሉ ኃይለማርያም ውል ያደሱ ተጫዎቾች ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ