የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባህር ዳር ገብቷል

ነገ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ኮትዲቯርን የሚገጥሙት ዋሊያዎቹ ከአንድ ሰዓት በፊት ባህር ዳር ደርሰዋል።

ከትላንት በስትያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማዳጋስካርን የገጠሙት ዋሊያዎቹ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ነገ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም 10:00 ላይ ያከናውናሉ። ለዚህ ጨዋታ ቡድኑ ትላንት አመሻሽ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ከአንድ ሰዓት በፊት ጨዋታው ወደሚደረግበት ከተማ ተጉዟል።

7:00 ሰዓት በባህር ዳር አየር ማረፊያ የደረሰው ቡድኑ በከተማው ደጋፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል። 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ወደ ባህር ዳር ያመራው ልዑካኑ ዋና አሰልጣኙን በበረራው እንዳላካተተ ተሰምቷል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከተጨዋቾቹ ጋር ወደ ባህር ዳር እይጓዙ እንጂ በቀጣይ በረራ ወደ ባህር ዳር እንደሚያመሩ ተሰምቷል።

ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ 11 ሰዓት ነገ ጨዋታውን በሚያከናውንበት ባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ቀለል ያለ ልምምዱን እንደሚሰራ ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጋጣሚ የሆነው የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን አመሻሽ ባህር ዳር እንደሚገባ ተሰምቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ከቡድኑ (ኮትዲቯር) ልዑካን በፊት አርብ ባህር ዳር የገባውን አስተባባሪ ጠይቆ እንደተረዳው ከሆነ ዝሆኖቹ ልምምድ ለመስራት እንዳላሰቡ ተጠቁሟል። ቡድኑ አመሻሽ ባህር ዳር ገብቶ፣ ነገ ጨዋታውን አከናውኖ በዛው ምሽት ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመራ ተገልጿል።

ከኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ የክሪስታል ፓላሱ የመስመር አጥቂ ዊልፍሬድ ዘሃ ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ተነግሯል።

ነገ 10:00 የሚደረገውን ጨዋታ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት (አማራ ቲቪ) በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ተጠቁሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ