“የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጎሌን ኮትዲቯር ላይ በማስቆጠሬ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ሱራፌል ዳኛቸው

ዛሬ በዋና ብሄራዊ ቡድን ደረጃ የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው ሱራፌል ዳኛቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር። በስታዲየሙም የነበረው ድባብ ለየት ያለ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ጨዋታው በውጤት የታጀበ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ።

ግብ በማስቆጠርክ ምን ተሰማህ?

የዛሬው ጎል በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያስቆጠርኩት የመጀመሪያ ጎሌ ነው። ይህንን ጎሌን ደግሞ ኮትዲቯሮች ላይ በማስቆጠሬ እጅግ ደስተኛ ነኝ። በዚህም ደግሞ ለየት ያለ ደስታ ተሰምቶኛል። በአጭሩ ከመጠን በላይ ደስ ብሎኛል።

ተጋጣሚያችሁን እንዴት አገኛችኋቸው?

መጀመሪያ የአፍሪካ ቡድኖች ጉልበት ላይ የተመረኮዘ ጨዋታ እንደሚጫወቱ እናውቅ ስለነበረ ስለእነሱ ግንዛቤው ነበረን። ቅዳሜም ማዳጋስካርን ሄደን አይተን ስለነበር የአፍሪካ ቡድኖችን አጨዋወት በደንብ አጢነናል። ከምንም በላይ ረጃጅም ኳሶችን እንደሚያዘወትሩ እናውቅ ስለነበረ ዝግጅት አድርገናል። እኛ ግን ኳስን መሰረት አድርገን የምንጫወት ስለሆነ አልከበደንም። ወደፊትም በእርግጠኝነት የምናገረው ማንም ቡድን በቀላሉ እንደማያሸንፈን ነው።

አሰልጣኛችው (አብርሃም መብራቱ) በጨዋታው የሰጧችሁ የቤት ስራን በአግባቡ ተወጥተናል ብለህ ታምናለህ?

አሰልጣኙ ከጨዋታው በፊት የሰጠንን ነገር በሚገባ አሳክተናል። እኛ ኳስን መስርተን ነበር የምንጫወተው፤ በዚህም ተጋጣሚያችንን በልጠናል። በአጠቃላይ ግን አሰልጣኛችን የሰጠንን የቤት ስራ በሚገባ ሜዳ ላይ ተግብረናል። ስራውም ፍሬ አፍርቶ አይታችኋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ