በታንዛኒያ አስተናጋጅነት እየተደረገ ያለው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ኢትዮጵያ ጅቡቲን 8-0፤ ኬኒያ ዩጋንዳን 3-0 አሸንፈዋል።
በታንዛኒያዋ ዋና ከተማ ዳሬ ሠላም ባለፉት ቀናት በስምንት ሀገራት መካከል ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የየምድቦቹ የመጨረሻ ጨዋታ ትላንት እና ዛሬ የተደረጉ ሲሆን ከምድብ አንድ ኬኒያ እና ዩጋንዳ፤ ከምድብ ሁለት ደግሞ ታንዛኒያ እና ቡሩንዲ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሸጋግረዋል፡፡ ትላንት በመጨረሻው ከምድብ ሁለት በተደረገ መርሀ ግብር ታንዛኒያ ዛንዚባርን 7ለ0 በመርታት ከምድቧ ዘጠኝ ነጥቦችን በመያዝ አንደኛ ሆና ማለፍ ስትችል ቡሩንዲ ደግሞ ደቡብ ሱዳንን 3ለ0 ረታ በስድስት ነጥቦች ሁለተኛ ሆና ፈፅማለች፡፡
ዛሬ ቀን 8:00 አስቀድመው መውደቃቸውን ያረጋገጡት ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ተገናኝተው ኢትዮጵያ 8ለ0 ረምርማለች፡፡ ለሉሲዎቹ ረሂማ ዘርጋው ሦስት ግቦችን አስቆጥራ ሐት-ትሪክ ሰትሰራ በዛሬው ጨዋታ አምበል የነበረችው ሽታዬ ሲሳይ ደግሞ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችላለች፡፡ ቀሪዎቹን ግቦች ሴናፍ ዋቁማ እና ገነሜ ወርቁ ያስቆጠሩ ሲሆን የጅቡቲዋ ተከላካይ ሱመያ አብዲ በራሷ ላይ ግብ ብታስቆጥርም ኳሷን አስቀድማ ወደ ግብ በመታችው ተከላካዩዋ ታሪኳ ዴቢሶ ተመዝቦ ኢትዮጰያ 8-0 በማሸነፍ ከምድቧ ያለምንም ነጥብ ከመሰናበት ተርፋ ሶስት ነጥብ ይዛ አጠናቃለች፡፡
ቀጣይ ጨዋታ ኬኒያ ጠንካራዋ ዩጋንዳን 3-0 አሸንፋለች፡፡ የኬኒያዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ ሜርሲ ኤሮ፣ ማዋሀሊማ አዳም እና ጀትሪክ ሺጋንግዋ የሀራምቤ ከዋክብትን ግቦች ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኬኒያ ሶስቱንም ጨዋታ አሸንፊ በዘጠኝ ነጥብ አንደኛ ሆና ስትፈፅም ተሸናፊዋ ዩጋንዳ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተያይዘው አልፈዋል፡፡
የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች
ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2012
ታንዛንያ ከ ዩጋንዳ
ኬንያ ከ ቡሩንዲ
*የኬንያዋ አጥቂ ጀንትሪክ ሺጋንግዋ በስድስት ግቦች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራች ትገኛለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ