የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ በኅዳር ወር መጨረሻ ይጀመራል

የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ሲታወቅ ቀደም ብሎ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓትም ይደረጋል፡፡

በርካታ ክለቦችን ተሳታፊ የሚያደርገው እና በስድስት ምድቦች ተከፍሎ የሚከወነው የዚህ ውድድር የ2012 የውድድር ዘመን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ህዳር 18 ከተደረገ በኋላ ህዳር 28 ውድድሩ እንዲጀመር የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ ወስኗል፡፡ ይሁንና የውድድሩ መጀመርያ ቀን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ከሚደርግበት ቀን ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የጅማሮው ቀንም በአንድ ሳምንት ሊራዘም የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተያያዘ በአንደኛ ሊግ ውድድሮች ከዚህ ቀደም ከየምድባቸው መጨረሻ ደረጃን የያዙ ክለቦች ሳይወርዱ በውድድሩ ላይ እየተሳፉ የሚዘልቁ የነበረ ሲሆን በ2011 የውድድር ዓመት ግን መጨረሻ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች ፌድሬሽኑ ባወጣው አዲስ ህግ መሠረት እንዲወርዱ ተደርጓል። ይህም ጉዳይ ለክለቦች አዲስ በመሆኑ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክለቦች ለፌዴሬሽኑ ቅሬታን አሰምተው ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ከፌዴሬሽኑ መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን እንዳገኘንም የምንገልፅ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ