የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን 2-1 በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ ለ6ኛ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የዕለቱ የክብር እንግዶች ከተጫዋቾች ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለውድድሩ ለሰጡት ድምቀት ከፌዴሬሽኑ የዕውቅና ዋንጫ እና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በዕለቱ በጣለው ዝናብ ምክንያት የአዲስ አበባ ስታዲየም ሜዳ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ለእንቅስቃሴ ፈታኝ የነበረ ሲሆን በተለይም ሰበታዎች ኳስ ከኋላ ጀምረው ለመጫወት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቅብብሎችን በማቋረጥና በፍጥነት ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመቀየር ስኬታማ አጋማሽ ማሳለፍ ችለዋል። በተለይም በሰበታ የግራ መስመር በኩል የነበረው የመከላከልም ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ የላላ የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ገና በ26ኛው ደቂቃ በቦታው የተሰለፈው ፍርዳወቅን አስወጥተው ናትናኤልን ለመተካት ተገደዋል።

በ16ኛው ደቂቃ ሰበታዎች ኳስ መስርተው ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ለመውጣት በሚሞክሩበት ወቅት ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ሙሉዓለም መስፍን ያቋረጠውን ኳስ ለአብዱልከሪም አቀብሎት የቀኝ መስመር ተከላካዩ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን አይቮሪኮስታዊው ዛቦ ቴጉይ በግንባሩ በመግጨት ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጊዮርጊሶች በጥሩ መነቃቃት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል መድረስ ሲችሉ ሰበታ ከተማዎች የተዳከመ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጎል ክልል የደረሱባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ጥቂት የነበሩ ሲሆን ሊጠቀስ የሚችል ለጎል የቀረበ ሙከራም ማድረግ አልቻሉም።

ጨዋታው በዚህ ሒደት ቀጥሎ በ39ኛው ደቂቃ አቡበከር ሳኒ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ከሰበታዎች የነጠቀውን ኳስ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት ወደ ሰበታ የጎል ክልል በመግባት ዛቦ ቴጉይ ያሻገረለትን ኳስ ሳላዲን ሰዒድ ወደ ጎል ሲመታው በደሳለኝ ደባሽ ተጨርፎ ሁለተኛ ጎል በመሆን ተመዝግቧል። ይህ ጎል ሳላዲን ሰዒድ በ4 ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ እንዲያጠናቅቅም አድርጎታል።

ከእረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ አድርገው የገቡት ሰበታዎች እንደከዚህ ቀደም ጨዋታዎች ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽ እጅጉን ተሻሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለጎል የቀረቡ ተደጋጋሚ ሙከራዎችንም አድርገዋል። በተለይም ፍፁም ገብረማርያም ተቀይሮ ከገባ በኋላ በግሉ ያደረገው ጥረት ለሰበታ በዚህ አጋማሽ መሻሻል ጎላ ሚና ተጫውቷል።

በ52ኛው ደቂቃ ፍፁም በሳጥን ውስጥ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ወደ ጎል ከመሞከሩ በፊት አስቻለው ታመነ በአስደናቂ ሁኔታ ሸርተቴ ወርዶ ያወጣበት እና በ56ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ በግራ መስመር በኩል ከርቀት አክርሮ መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራዎች ሰበታዎች በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያቃረባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በ57ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም ከተከላካዮች አምልጦ ወደ ግብ ክልል በሚያመራበት ወቅት ፍሪምፖንግ ሜንሱ ጠልፎ በማስቀረቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱ ደግሞ ይበልጥ ሰበታ ከተማ ጫና ፈጥሮ እንዲጫወት በር ከፍቶለታል።

የሰበታ ጫና ቀጥሎ በ71ኛው ደቂቃ ዳዊት በቺፕ ያቀበለውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በደረቱ ካበረደ በኋላ ወደ ጎል መትቶ ባህሩ ነጋሽ እና የጎሉ ቋሚ በመለሰበት ኳስ ሰበታ ከተማ ጎል ለማስቆጠር በእጅጉ የቀረበበት ነበር። በ82ኛው ደቂቃም ተደጋጋሚው ጫና ፍሬ አፍርቶ ከግራ መስመር ከጌቱ ኃይለማርያም ተሻገረውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በግምባሩ በመግጨት ወደ ጎልነት ቀይሮ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሰበታዎች የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን በማብዛት ጫና መፍጠሩን ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጥብቅ መከላከል ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ90ኛው ደቂቃ ፍፁም ከመስመር የተሻገረለትና ገጭቶ ባህሩ ነጋሽ ከያዘበት ሙከራ ሌላ ተጨማሪ ክስተት ሳንመለከት ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከድሉ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለስድስተኛ ጊዜ ያሸነፉት ውድድሩ ዋንጫን ከአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ እጅ ሲቀበሉ የአብስራ ተስፋዬ የዕለቱ የጨዋታ ኮከብ ተብሎ ተመርጧል። የውድድሩ ኮከቦች ሽልማት ደግሞ በቀጣይ በሚደረግ ልዩ ሥነ-ስርዓት ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።


© ሶከር ኢትዮጵያ