“የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ሦስቴ በማንሳት ሐት-ትሪክ መስራቴ ደስተኛ አድርጎኛል ” ሥዩም ከበደ


ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለድሎቹ ፋሲል ከነማዎች የሊጉ ሻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 ካሸነፉ በኃላ አዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታውን እንደተመለከታችሁት በመጀመርያው አጋማሽ ላይ በመጠኑ በመሐል ሜዳ ላይ በመቐለ በኩል ደህና ነገር አይቼባቸዋለው። ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ግን በእኛ በኩል ማስተካከያዎች በማድረግ የተሻለ ብልጫ ወስደን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መጠቀም አልቻልንም። እንደዚያም ቢሆን ቡድናችን ከእረፍት መልስ ባደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አንድ ጎልም ቢሆን አስቆጥረን ለማሸነፍ በመቻላችን በጣም ደስ ብሎኛል።”

የዋንጫው አስፈላጊነት

” ባለፈው ዓመት እንደምታውቁት ቡድኑ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ ድረስ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ትልቅ ተጋድሎ አድርጎ ፍፃሜው ላይ ነው ዝቅ ብሎ ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀው። በወቅቱ ብዙ ያለፉ ነገሮች ነበሩ፤ እርሱን ወደ ኃላ ተመልሶ ማሰብ አያስፈልግም። ለተጫዋቾቹ፣ ለደጋፊዎች እና ለሁሉም ይህ ዋንጫ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የትናንትናው ጨዋታ ፕሮግራም ከወጣ ጀምሮ አሸናፊ ሆነን ለማጠናቀቅ ሰፊ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል። በእውነት ስለተሳካልኝ ተጫዋቾቼ፣ ደጋፊዎች ሁላችሁንም እንኳን ደስ አለን ማለት እፈልጋለው። ይህ ድል ለእኔ በግሌ ለ2012 የውድድር ዘመን ትልቅ መነሳሳት ይሆነኛል።

ሦስተኛ ክብር

“አስቀድሞ በ1995 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር፣ ዓምና ከመከላከያ ጋር፣ ዘንድሮ ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ሦስቴ በማንሳት ሐት-ትሪክ በመስራቴ በግሌ በጣም ደስተኛ አድርጎኛል። አሰልጣኝ ሆነህ እንዲህ ያሉ በዋንጫ የታጀበ ስኬት ሲኖርህ ክብር ነው። ይህ ስኬት ለቀጣይ ስራዬ ትልቅ መነሻ ነው ብዬ አስባለው።”

ቀጣይ…

” እኔ ምን እንደምፈልግ፤ ቡድኑም ምን እንደሚፈልግ አውቃለው። የእኔ የእግርኳስ እምነቴ ደግሞ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ከውጤት ጋር ሲሆን ነው እርካታዬ። ይህን በቡድኑ ውስጥ ለማስቀጠል አጥቂ ስፍራ ላይ ያሉ ተጫዋቾች ይህን ለማድረግ አቅም አላቸው። የኳስ ቁጥጥር ትርጉም ባለው መልኩ የበለጠ እያሳደግነው ከውጤት ጋር በመሄድ እንሞክራለን። የ2012 የውድድር ዘመን በድል ለማጠናቀቅ አጠቃላይ የቡድኑ አባላት ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ