በነገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ እና የደጋፊዎች ጥምረት ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

መረጃው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው።

የደጋፊዎች ጥምረት እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህንጻ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ” የደጋፊዎች ጥምረት ለማቋቋም የተጀመረው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህም የተሻለ የውድድር ጊዜ እንዲኖር የሚያደርግ ነው የነገውን የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ትልቅ መልዕክት የምናስተላልፍበት እንዲሆን እንፈልጋለን። በየክልሉ የተደረጉት የሲቲካፕ ጨዋታዎች በመልካም ሁኔታ ነው የተጠናቀቁት ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ መልካም ስራዎችን ተመልክተናል ይህንንም ወደ ሌሎች ማስቀጠል ይኖርብናል። ከአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድር መልካም ተሞክሮዎችን አይተናል በብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ወቅት የቲኬት አቆራረጥ ተሞክሮ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነን። ”

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ጋሻው አስማረ ” በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር እንደ ክለብ መልካም ስራዎች ደጋፊዎቻችን እንዲሰሩ ተዘጋጅተናል። ብዙም ተጓዥ ደጋፊዎች የሉንም፤ እንደ ሀገር ደጋፊዎች ጥምረት መኖሩ ብዙ መልካም ስራዎች እንዲሰሩ ያደርጋል”

መቐለ 70 እንድርታ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት አትክልቲ ሀይለስላሴ ” ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመዘገብ የመጣችሁ ሚዲያዎችን አመሰግናለሁ። እንዲሁም የደጋፊዎችን ጥምረት ለመመስረት የሰነድ ጥናት ለምታደርጉ ትልቅ ምስጋና አለኝ። እኛ ከየትኛውም ክለብ ጋር ችግር ውስጥ መግባት አንፈልግም የመቐለ 70 እንድርታ ድጋፊ በሁሉም ቦታ በመሄድ ቡድኑን እንዲያበረታታ እንፈልጋለን”

ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸው ጋዜጣዊ መግለጫው ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ