በነገው ዕለት በዐፄዎቹ እና በምዓም አናብስት መካከል የሚካሄደውን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው መቐለ 70 እንደርታ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ፋሲል ከነማ የሚያገናኛው ይህ ጨዋታ ማራኪ ፉክክር እና ጥሩ ጨዋታ ይታይበታል ተብሎ ይገመታል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከሌሎች ክለቦች አንፃር ሲታይ ብዙም ተሳትፎ ያላደረጉት እና በአዳማ ከተማ ዋንጫ ተሳታፊ የነበሩት ዐፄዎቹ በውድድሩ በአመዛኙ ከባለፈው ዓመት ስብስብ ጋር የሚመሳሰል ቡድን ይዘው ነበር የቀረቡት።

ባለፈው ዓመት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር በዋነኝነት በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው እንደየተጋጣሚያቸው የመከላከል አቀራረብ የሚቀያየር ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በዚህ የውድድር ዓመት ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ሰጥተው ለመጫወት በመሞከር ላይ ይገኛሉ።

በአዳማ ዋንጫ በዋነኝነት እንየው ካሳሁን በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ለማጥቃት ሲሞክሩ የታዩት ፋሲሎች በውድድሩ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ብዙ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በዚህም ከአዲሱ ፈራሚያቸው መልካሙ ታውፈር ውጭ ሙሉ ቡድኑ በጥሩ ጤንነት ይገኛል።

ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ቀድመው የገቡት እና በዝግጅት ላይ በርካታ ጊዜያቸውን ያሳለፉት መቐለዎች የቅድመ ውድድር ጊዜያቸውን በትግራይ ዋንጫ እና ሌሎች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በማድረግ ነበር ያሳለፉት። በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙ ሲሆን በትግራይ ዋንጫ በተከተሉት አጨዋወት መሰረት የጨዋታ አቀራረብ ላይ ብዙም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በቅጣት እና በጉዳት በማጣታቸው በርካታ የተጫዋቾች ለውጥ ማድረጋቸው ግን አይቀሬ ነው።

ከባለፈው ዓመት የአማካይ ምርጫቸው ሐይደር ሸረፋ እና ጋብርኤል አሕመድን ወደ ሌላ ክለብ በመሸኘታቸው፤ ሚካኤል ደስታ እና ዮናስ ገረመውን በጉዳት ምክንያት ያጡት መቐለዎች ባለፈው ዓመት ከነበረው ፈጠራ የተሞላበት እና አናሳ የመከላከል አቅም ያለው የአማካይ ክፍል ለየት ያለ አቀራረብ ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ያሬድ ከበደ ከተፈጥሯዊ ቦታው ወደ ኃላ ተስቦ ይጫወታል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ውጭ ሁለት የመሃል ተከላካዮች ያጡት መቐለዎች ዳንኤል ደምሱን በመሃል ተከላካይነት ሊያሰልፉ እንደሚችሉም ይገመታል።

መቐለዎች በትግራይ ዋንጫ በአብዛኛው ተቀራራቢ አጨዋወቶች መርጠው የገቡት ሲሆን በነገው ጨዋታ በሁለቱም የአጥቂ ጥምረቶች መሰረት ያደረገ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የመስመር አጨዋወትም ቡድኑ በአማራጭነት የሚይዘው ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ይገመታል።

ምዓም አናብስት በዚ ጨዋታ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ሚካኤል ደስታ፣ ዮናስ ገረመው፣ ታፈሰ ሰርካ፣ አሚን ነስሩ በጉዳት ሲያጡ ኦኪኪ ኦፎላቢ አፎላቢ (ዐምና በ29ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ) እና ሥዩም ተስፋዬ (ዐምና 29ኛው ሳምንት ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ) በቅጣት አይሰለፉም። አዲስ ፈራሚው ላውረንስ ኤድዋርዶም በአንዳንድ የውል ጉዳዮች ምክንያት ለጨዋታው አይደርስም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ
(4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ – ጋብሬል አህመድ

ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – ኦሲይ ማዊሊ

ሙጂብ ቃሲም

መቐለ 70 እንደርታ

(4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

አሸናፊ ሃፍቱ – ዳንኤል ደምሱ – አሌክስ ተሰማ – አስናቀ ሞገስ

ኤፍሬም አሻሞ – ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ – ሄኖክ ኢሳይያስ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገ/ሚካኤል – ያሬድ ብርሃኑ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ