ወልቂጤ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ታውቋል

በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመሳተፍ እየተዘጋጀ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ በመክፈቻው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥምበት ሜዳ ታውቋል።

የወልቂጤ ስታዲየምን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች እየተከወኑ ቢገኙም ግንባታቸው በሚጠበቀው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ለተወሰኑ ወራት በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በተቀያሪ ሜዳ እንዲያደርጉ በፕሪምየር ሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ክለቡ የስታዲየሙን የመጫወቻ ሜዳ ሳር ለማልበስ የቁፋሮ ስራዎችን አጠናቆ በቅርቡ ሳር ማልበስ የጀመረ ሲሆን የሳሩ እድገት ከሚፈጀው ጊዜ አንፃር ሜዳው ለሊጉ ጅማሮ የማይደርስ በመሆኑ በአማራጭነት በተመዘገበውና ከወልቂጤ 152 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው የባቱው ሼር ስታዲየም ላይ ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።

ወልቂጤዎች የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታቸውን በአንደኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባቱ ላይ የሚያከናውኑ ሲሆን በ3ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ሜዳቸው እንደሚደርስ በባለሙያ እንደተገለፀላቸው ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ