አንጋፋው የድሬዳዋ ስታዲየም ከአንድ ዓመት በላይ ሲደረግለት የነበረው የማስፋፊያ እና የማሻሻያ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረሰ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የ1968 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ ስታድየም ለወራት የማስፋፊያ እና እድሳት ሲደረግለት በመቆየቱ እና ግንባታው በፍጥነት ባለመጠናቀቁ ድሬዳዋ የ2012 የውድድር ዘመንን ጨዋታዎቹን በሁለተኝነት ባስመዘገበው ሐረር ስታድየም እንዲጫወት አስቀድሞ ውሳኔ መሰጠቱ ይታወቃል።
በኮሚሽነር ዓና ዑመር የሚመራው የድሬደዋ ስፖርት ኮሚሽን ባደረገው እንቅስቃሴ በአሁን ወቅት አብዛኛው የስታዲየሙ ማስፋፊያ እና የእድሳት ስራ እየተጠናቀቀ ይገኛል። በዚህም መሠረት ተመልካቹን ከተጫዋቾች የሚለየው አጥር ተሰርቶ ተጠናቋል፣ የስታዲየሙ ዙርያ መቀመጫ ሙሉ ለሙሉ በወንበር እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳውም ለጨዋታ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ያልነበረ በተለምዶ ከማን አንሼ በሚባለው በቀኝ አቅጣጭ 500 ሰው የመያዝ አቅም ያለው አዲስ የስቴዲየም ክፍል ከነ ሙሉ ወንበር መቀመጫው ተገንብቶ ተጠናቋል። በቀሩት ቀናትም በስተግራ ያለው ከማአን አንሼ ግንባታ እንደሚጠናቀቅ ሰምተናል።
የሜዳውን ጥራት እና ጨዋታ ለማጫወት ያለውን ዝግጁነት አወዳዳሪው አካል ከገመገመ በኃላ ድሬደዋ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ እንዲጫወት ማረጋገጫ ሰጥቶታል። በዚህም መሠረት ድሬደዋ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች እንዳጋጣሚ ሆኖ ከሜዳው ውጭ ከሀዋሳ ከተማ እና ከፋሲል ከነማ ጋር ከተጫወተ በኃላ የመጀመርያ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ታኀሳስ ወር ላይ እንደሚያደርግ ታውቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ