የአንደኛ ሊግ የ2012 ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ተካሄደ

በዛሬው ዕለት በራስ ሆቴል በተካሄደው መርሃግብር የ2011 የውድድር ዘመን ግምገማና በመጪው ታህሳስ 5 የሚጀምረው የአዲሱ የውድድር ዘመን የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።

መርሐግብሩን በክብር እንግድነት በመገኘት በንግግር ያስጀመሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አደራ አዘል መልዕክት አስተላፈዋል።

በመቀጠልም ተሳታፊ ከሆኑት 60 ክለቦች መካከል 41 ክለቦች መገኘታቸው በመረጋገጡ መርሐግብሩ እንዲቀጥል ተደርጓል።

በመቀጠልም የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ፀሀፊ በሆኑት አቶ አላዩ አማካነት የ2011 የውድድር አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርቱ በርካታ የተለመዱ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በተለይም በክለቦች በኩል የሚስተዋለው የኢሜይል አጠቃቀም አናሳ መሆኑ እንደ ተግዳሮት በስፋት ተነስቷል።

በመቀጠል በቀረበው ሪፖርትና ስለ አዲሱ የውድድር ዘመን ደንብ ዙሪያ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ከዓመታዊ ክፍያ፣ ምድብ አደላደልና መርሃግብር አወጣጥ እንዲሁም ከሊጉ ስያሜና የሚዲያ ሽፋን ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ሀሳቦች ተነስተዋል። በተጨማሪም በሊግ ኮሚቴው በቀረበው የማጠቃለያ ውድድርን በማስቀረት ከየምድቡ አንደኛ የወጡ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ በቀረበው ሀሳብ ዙርያ በርካታ ሀሳቦች ሀሳቦች በሁለቱም ፅንፍ ተነስተዋል።

በማስከተል በተነሱት ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸው የፌደሬሽኑ እንዲሁም የሊጉ የበላይ ሀላፊዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ውድድሩ ህየኅዳር 28 ይጀመራል ቢባልም የውድድሩ ጅማሮ ከፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤየዔ ጋር ቀኑ በመገጣጠሙ የውድድሩ ጅማሮ ወደ ታህሳስ 5 ስለመቀየሩ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። ተያይዞም የማጠቃለያ ውድድሩ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል።

በስተመጨረሻ በሊግ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ከነበረው የምድብ ድልድል የተለየ ወጪ ቁጣቢ የሆነና ክለቦችን በቅርብ ካሉ አጎራባች ክለቦች ጋር የቀረበው አማራጭ ሀሳብ በአዲስአበባ ክለብ ተወካዮች ዘንድ ከአጠቃላይ የስፖርቱ መርህና በክልሎች መካከል ያለውን አብሮነት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል ተብሎ በቀረበው ተቃውሞ ድልድሉ ከዚህ ቀደም በነበረው መልኩ እንዲቀጥል ተወስኗል። ለአዲሱ አማራጭ የድልድል ሀሳብ ተግባራዊ መደረግ አፅንኦት ሰጥተው ሲከራከሩ የነበሩት የትግራይ ክልል ተወካይ ክለቦችም ውሳኔውን በመቃወም የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርአቱን ረግጠው ወጥተዋል።

የውድድሩ ምድብ ድልድል ይህንን ይመስላል


© ሶከር ኢትዮጵያ