ነገ በትግራይ ስታዲየም በዝግ የሚካሄደው ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በትግራይ ስታዲየም የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ምንም እንኳ ለደጋፊዎች ክፍት ባይሆንም ሁለቱም ክለቦች ባላቸው የጨዋታ አቀራረብ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እያሳዩ የሚገኙት መቐለዎች ምንም እንኳ አሁንም የአጥቂያቸው ኦኪኪ ኦፎላቢ እና የተወሰኑ ተጫዋቾች ግልጋሎት ባያገኙም ጨዋታው በሜዳቸው እንደመሆኑ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። በትግራይ ዋንጫ ጨምሮ ከፋሲል ጋር በነበረው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታም ከሌላው ጊዜ በተለየ በመስመር ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው መቐለዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይዘው ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ቡድኑ አዲስ ባዋቀረው የአማካይ ጥምረት የተሻለ የፈጠራ አቅም ጨምሮ ሌላ የማጥቅያ አማራጭ የሚፈጥርበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።
ቡድኑ አምበሉ ሚካኤል ደስታን በጉዳት፣ ኦኪኪ ኦፎላቢን በቅጣት ሲያጣ ሥዩም ተስፋዬ ቅጣቱ ጨርሶ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አዳጊዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአዳማ ከተማ እስከ ፍፃሜ በነበራቸው ቆይታ ተለዋዋጭ በሆነ የጨዋታ አቀራረብ ሲያስፈልግ መሀል ለመሀል በሚደረጉ የአንድ ሁለት ቅብብሎች አልያም ከተከላካዮች በቀጥታ በሚላኩ ኳሶች የግብ እድሎችን ለመፍጠር የሚሞክር ቡድን መሆኑን አስመልክቷል።
ቡድኑ ለአጫጭር ቅብብሎች የተመቹ እንደነ በኃይሉ ተሻገር እና ይሁን እንደሻውን የመሳሰሉ አማካዮች እዩኤል ዘሪሁንና ቢስማርክ አፒያ አይነት ፈጣን የመስመር ተጫዋቾችን ጨምሮ በአየር ላይ ኳሶችን በማሸነፍ ውጤታማ የሆነው ሙሳ ካማራን በፊት መስመራቸው ላይ መያዛቸው ቡድኑ ተገማች እንዳይሆን ይረዱታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሀዲያዎች አማካያቸው ሱራፌል ጌታቸውን በጉዳት ስያጡ የደስታ ጊቻሞ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በፕሪምየር ሊጉ ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል።
– ከዚህ ቀደም በ2009 በከፍተኛ ሊግ መለያ ጨዋታ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ድሬዳዋ ላይ ተገናኝተው መቐለ 2-1 አሸንፎ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገበት ጨዋታ በሁሉም ውድድሮች የመጨረሻ ግንኙነታቸው ነው።
– በነገው ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖችን ጎል ይጠብቃሉ ተብሎ የሚጠበቁት የኢኳቶሪያል ጊኒያዊያኑ ወንድማማቾች ፊሊፕ ኦቮኖ እና አቤር ኦቦኖ በኢትዮጵያ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ በተቃራኒ ይፋለማሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)
ፍሊፕ ኦቮኖ
ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – አስናቀ ሞገስ
ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሱ
ኤፍሬም አሻሞ – ያሬድ ከበደ – ሳሙኤል ሳሊሶ
አማኑኤል ገ/ሚካኤል
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
አቤር ኦቮኖ
ትዕግስቱ አበራ – አዩብ በቀታ – በረከት ወልደዮሀንስ – ሄኖክ አርፊጮ
ይሁን እንደሻው – አብዱልሰመድ ዓሊ – አፈወርቅ ኃይሉ
በኃይሉ ተሻገር – ቢስማርክ አፒያ – ሙሳ ካማራ
© ሶከር ኢትዮጵያ