ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ከ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታዎች መካከል ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀው የአዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በ9:00 አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ይደረጋል።

በአዲስ አሰልጣኞች የሚቀርቡት ሁለቱ ቡድኖች በክፍተቶቻቸው ላይ ካሟላቸው አዳዲስ ተጫዋቾች በቀር ብዙም ለውጥ ያልተደረገበት ቡድን ይዘው ዓመቱን የሚጀምሩ እንደመሆኑ ከመክፈቻዎቹ ጨዋታዎች መካከል ያልተቀዛቀዘ እና ጥሩ እንቅስቃሴ የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የቀድሞ አሰልጣኛቸው አሸናፈ በቀለን በድጋሚ የቀጠሩት አዳማዎች አማካይ ክፍል ላይ ለተለያዩ ዓይነት አጨዋወት የሚሆኑ በርከት ያሉ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎችን በቡድናቸው ይዘዋል። በአዳማ ከተማ ዋንጫም ላይ ከቡድኑ ወሳኝ የመሀል ሜዳ ተሰላፊ ከነዓን ማርክነህ ውጭ ያላቸውን አማራጮች በአዳማ ከተማ ዋንጫ ላይ በስፋት ለመልከት ሞክረዋል።

ቡድኑ አመዛኙ ፈጥን ባሉ ሽግግሮች ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች ተቀዳሚ የግብ እድል መፍጠሪያ አማራጮቹ ሲሆኑ ለመስመር ተከላካዮቹም በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ ነፃነት በመስጠት እንዲያጠቁ እንደሚፈቅዱ ተስተውሏል። ሁለት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን የተከላካይ አማካዮችን መጠቀሙ በመልሶ ማጥቃት የሚፈጠር ተጋላጭነትን በመቀነስ ረገድ የተሻለ ያደርጋቸዋል።

በቡድን ዜና ረገድ አደማ ከተማ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ የተሟላ ቡድኑን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል።

በሥዩም ከበደ እየተመሩ አዲሱን የውድድር ዘመን መቐለን 70 እንደርታን በመርታት የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በማንሳት የጀመሩት ፋሲል ከተማዎች ከዐምናው የውበቱ አባተ ስብስብ በተጫዋቾች ደረጃ እምብዛም ለውጦች ባይኖሩም አምና ከነበራቸው ተለዋዋጭ አቀራረብ በተለየ ዘንድሮ ኳስን ይበልጥ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።

ቡድኑ ከነበረው አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩ ሽግግር ላይ በመሆኑ በተለይ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ በበርካታ አጋጣሚዎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ወቅት ኳስን መስርተው ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ በተቃራኒ ተጫዋቾች ጫና በርከት ያሉ የቅብብል ስህተቶች እንዲሁም ኳሶች ሲነጠቁ ተስተውሏል። በአዳማ ከተማ ዋንጫ ቡድኑ እንየው ካሣሁንና ሽመክት ጉግሳ በሚሰለፉበት ቀኝ መስመር ይበልጥ በማጥቃቱ አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውሏል።

የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሳሁን በትከሻ ውልቃት ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ በመራቁ የዐምናው የቡድኑ ተመራጭ ሰዒድ ሀሰን ክፍተቱን የሚሸፍን ይሆናል። ሰዒድ በመቐለው ጨዋታ ሙጂብ ባስቆጠራት ግብ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሪከርዳቸውም ተመጣጣኝነት ይስተዋልበታል። አንድ አንድ ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን ሌሎቹ አምስት ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ናቸው። በሰባቱ ግንኙነታቸውም እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ዘንድሮ አዳማ ላይ በተደረገው የአዳማ ከተማ ዋንጫ ሁለቱ ቡድኖች ለደረጃ ጨዋታ ተገናኝተው አዳማ ከተማ በመለያ ምቶች ማሸነፉ ይታወሳል።

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – መናፍ ዐወል – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – ከነዓን ማርክነህ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሳማኬ ሚኬል

ሰዒድ ሀሰን -ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ሱራፌል ዳኛቸው – ጋብሬል አህመድ – በዛብህ መለዮ

ሽመክት ጉግሳ – ሙጂብ ቃሲም – ኦሰይ ማውሊ


© ሶከር ኢትዮጵያ