ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

በመክፈቻው ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ተቀራራቢ የሆነ የጨዋታ አቀራረብ ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በሜዳም ከሜዳ ውጪም ባለው የደርቢት ስሜት ምክንያት ተጠባቂ ነው።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ አዲስ ቡድን በመስራት ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በትግራይ ክልል ዋንጫ እንደተከተሉት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እና በግብ ማስቆጠር ላይ ያለውን ችግር ፈትቶ ወደ ወሳኙ ጨዋታ መቅረብ ግድ ይለዋል።

የጦና ንቦች በትግራይ ዋንጫ ከፍፃሜው ጨዋታ ውጪ የተሳካ ጊዜ የነበራቸው ሲሆን በውድድሩ የተለያዩ ተጫዋቾች እና አጨዋወቶችን አቀያይረው ቢሞክሩም የነገው ጨዋታ ግን በሜዳቸው እንደመሆኑ አሰልጣኙ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ቡድን ይዘው የሚገቡበት ዕድል የሰፋ ነው።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ በትግራይ ዋንጫ ጉዳት ያጋጠመው አማካዩ በረከት ወልዴ ከጉዳቱ ባለማገገሙ አያሰልፍም።

በቅድመ ውድድር ላይ የትግራይ ዋንጫ አንስተው በጥሩ መነቃቃት ላይ ያሉት ሲዳማ ቡናዎች በክረምቱ በርካታ ለውጥ አለማድረጋቸውና በቅድመ ውድድር ላይ ያሳዩት ብቃት ተደማምሮ ዘንንሮም ለዋንጫ የሚገመት ቡድን ይዘው ነው ወደ ውድድር የሚገቡት።

ቡድኑ ባለፈው ዓመት በመስመሮች ላይ ያተኮረው አጨዋወቱ ላይ የተወሰነ የአቀራረብ ለውጥ ማድረጉ የታየ ሲሆን በቅድመ ውድድር ላይ በቡድኑ ውስጥ ያልነበረው ፈጣኑ የመስመር ተጫዋቻቸው አዲስ ግደይ ወደ ቡድኑ በመመለሱ እና ጨዋታው ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉት እንደመሆኑ የሚያጠቁበት መንገድን በተለመደው መልኩ ይቃኙታል ተብሎ ቢጠበቅም በትግራይ ዋንጫ ለኳስ ቁጥጥር ቅድምያ ሰጥቶ ለመጫወት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ፍንጭ አሳይቷል።

ሲዳማ ቡናዎች በነገው ጨዋታ የግራ መስመር ተከላካዩ ሚልዮን ሰለሞንን ግልጋሎት አያገኙም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 12 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ስድስት ጊዜ አሸንፏል።

– በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 18 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 6፣ ሲዳማ ቡና 12 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

– ወላይታ ድቻ በ2007 ካገኘው የ2-1 ድል ወዲህ በሊጉ ያለፉት ዘጠኝ ግንኙነታቸው ሲዳማን አሸንፎ አያውቅም።

– በሁሉም ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በዚህ ወር መጀመርያ በትግራይ ዋንጫ ፍፃሜ ሲሆን ሲዳማ ቡና 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

– ባለፈው ዓመት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም መከናወናቸው ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

አዛርያስ አቤል – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – እዮብ ዓለማየሁ

ተስፋዬ አለባቸው

ዘላለም ኢያሱ – እንድሪስ ሰዒድ – ነጋሽ ታደሰ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍስሀ – ግርማ በቀለ – ጊት ጋትኮች – ክፍሌ ኪያ

ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየሁ ዮሐንስ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – አዲስ ግደይ

ይገዙ ቦጋለ


© ሶከር ኢትዮጵያ