ጌታነህ ፣ ሽመልስ እና ኡመድ በዚህ ሳምንት . . .

 

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ጌታነህ ከበደ ክለቡ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በፕላቲኒየም ስታርስ 2-0 በተሸነፈበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል፡፡

ጌታነህ ዝዋንን በ63ኛው ደቂቃ ቀይሮ ገብቶ የአማተክስን ፊት መስመር ከባሴላ ጋር በመጣመር ቢመራም ክለቡ አማተክስን ከሽንፈት መዳን አልቻለም፡፡ የፕላቲኒም ስታርስን የድል ግቦች ሰለሞን ማቴ እና ሲያቦንጋ ዙሉ ለመረብ አሳርፈዋል፡፡

አማተክስ በሳለፍነው ሳምንት አሰልጣኝ ሳሚ ትሮተንን አሰናብቶ በምትክ የቀድሞ የባፋና ባፋና ኮከብ ሾን ባርትሌትን መቅጠሩ ይታወሳል፡፡ ባርትሌት ከዚህ ቀደም ጎልደን አሮስን እየመሩ ወደ አብሳ ፕሪምየርሺፕ አሳድገዋል፡፡

16 ክለቦች በሚወዳደሩበት የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሺፕ አማተክስ በ12 ነጥብ 15ኛ ሲሆን ሊጉን ማሜሎዲ ሰንዳውን በ39 ነጥብ ይመራል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ካይዘር ቺፍስ 4ኛ ሲሆን የ2015 የካፍ ኮንፌድሬሽ ዋንጫ የፍፃሚ ተፋላሚ የነበረው ኦርላንዶ ፓይሬትስ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የ17ኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይደረጋሉ፡፡ የሽመልስ በቀለ ክለብ የሆነው ፔትሮጀት ኢትሃድ አል ሻርታ ጋር ሲገናኝ ኡመድ ኡኩሪ የሚጫወትበት ኢኤንፒፒአይ ምስር አል ማቃሳን ያስተናግዳል፡፡ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያውን መከላከያ የሚገጥመው ምስር አል ማቃሳ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል

ያጋሩ